ቀጥታ፡

የአረቡ ዓለም ከግብፅ ምን አተረፈ?

የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አካሄድ በታሪካዊ እውነታዎች እና በኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ እየተመሠረተ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፣ ጊዜ ያለፈባቸው የጂኦ ፖለቲካዊ የመጠላለፍ አካሄዶች ዋጋ ቢስነትና ጥቅም አልባነት በግልጽ እየታየ ይገኛል።
 
ለብዙ አስርት ዓመታት ግብፅ የዓረብ ሊግን ለራሷ ጠባብ ፍላጎቶች እና ጂኦፖለቲካዊ አጀንዳዎች ማስፈጸሚያነት በሰፊው ስትጠቀምበት ቆይታለች።
 
ሆኖም ይህ ጥቅምና ጉዳትን ብቻ መሰረት ያደረገ ግንኙነት አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፦

ለመሆኑ የዓረቡ ዓለም ከግብፅ በምላሹ ያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?
 
ለዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ ምንም የሚል ነው ሲል  “What Has the Arab World Gained from Egypt?  Why Ethiopia Belongs in the Arab League?” ፀሐፊው እና በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ በቋሚነት አስተያየት የሚሰጠው ጅብሪል ላሞ በኢዜአ እንግሊዘኛ ገጽ ባሳፈረው ሐተታ ላይ የግብጽ ፖሊሲዎች እንዲሁም ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀው አምባገነናዊ አስተዳደር የጋራ ጥንካሬን ከመፍጠር ይልቅ የቀጣናውን አለመረጋጋት ማባባሳቸውን ገልጿል።
 
እነዚህ ፖሊሲዎች፣ በምሥራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባሕር አካባቢም ውጥረትን እያባባሱ እንደሚገኙ አመልክቷል።
 
እነዚህ አካባቢዎች ለዓረቡ ዓለም የራቁ አይደሉም፤ ይልቁንም ለዓረቡ ዓለም ደኅንነት፣ የባሕር ንግድ፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም የምግብ ዋስትና እጅግ ወሳኝ እና ስትራቴጂካዊ ማዕከላት ናቸው።
 
የግብፅ ከፋፋይ ቀጣናዊ አካሄድ ከታዩባቸው ጉልህ ማሳያዎች አንዱ በኤርትራ ጉዳይ እና በሰፊው የኢትዮጵያ ግዛት አንድነት ላይ የነበራት ታሪካዊ ጣልቃ ገብነት ነው። ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ቀጣናዊ ተፅዕኖዋን ለመግታት በግብጽ ታስበው የተደራጁ ተገንጣይ ኃይሎችን እና ፖለቲካዊ ፕሮጀክቶችን በግልጽ እንደምትደግፍ ፀሐፊው አውስቷል።
  
ከኢትዮጵያ የኤርትራ መገንጠል በምሥራቅ አፍሪካ ቀውስ የተሞላ ታሪክ ውስጥ አቢይ ክስተት ሲሆን፣ የውጭ ጂኦፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቶች የሀገራትን እጣ ፈንታ እንዴት እንደሚያናጉ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
 
የዲፕሎማሲ ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ቡትሮስ ቡትሮስ-ጋሊ፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም ታስቦ የተዘረጋውን የኤርትራን የመገንጠል ፕሮጀክት በመደገፍና በማፋጠን ረገድ ትልቅ ሚና ነበራቸው።
 
በተጨማሪም ግብጽ በደቡባዊ የቀይ ባህር ቀጣና የምታካሂደው ቀውስ የመፍጠር እንቅስቃሴ፣ ለዓለም አቀፍ የባህር ንግድና ለቀጣናው ደህንነት ቀጥተኛ ስጋት ደቅኗል። በባብ-ኤል-ማንደብ የባሕር ወሽመጥ አካባቢ ውጥረቶችን በመቀስቀስ እና ተላላኪ ታጣቂ ቡድኖችን በማንቀሳቀስ፣ ወሳኝ የሆኑ የባህር መተላለፊያዎችን የጂኦፖለቲካዊ ግጭት መድረክ አድርጋዋለች። ይህም ለጠቅላላው የዓረብ ዓለም የኢነርጂና የምግብ አቅርቦት መሰረት የሆነውን የደህንነት መዋቅር አደጋ ላይ ጥሎታል፤ ሲሉ ጅብሪል ላሞ ያብራራሉ።
 
ጅብሪል ላሞ በጽሑፉ ላይ እንዳሰፈረው፣ የግብፅ ግልጽ የራስ ወዳድነት እንቅስቃሴዎች ቀጣናዊ ውጥረትን የሚፈጥሩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ወደ ዓረብ ሊግ መቀላቀል ግን ለዓረቡ ዓለም እጅግ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ ለውጥ አምጪ ዕድል ይዞ ይመጣል።
 
በመደመር ፍልስፍና አሳታፊ ማዕቀፍ ሥር፣ ኢትዮጵያ ከማግለል ፖሊሲ ይልቅ የዓረቡን ዓለም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተሳሰር የሚያስችል የላቀ የዲፕሎማሲ አቅም አላት።
 
በዚህም የአፍሪካ ዋነኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የባለብዙ ወገን ትብብሮችን በመቅረጽ ረገድ ያላትን የካበተ ልምድ ታካፍላለች።
 
የኢትዮጵያ ወደ ዓረብ ሊግ የመቀላቀል ጥረት ጊዜያዊ የፖለቲካ ስሌት ሳይሆን፣ የተፈጥሮ የታሪክ ጥሪ ነው። ከ135 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ጥልቅ የሥልጣኔ መሠረት ያላት ይህች የቀይ ባሕር ሀገር፣ አባልነቷ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ስትራቴጂካዊ ድልድይ ይፈጥራል።
 
ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ያላት ቁርኝት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በጋራ ታሪክ፣ ባህል እና የደም ትስስር ላይ የተገነባ ነው።
 
እንደ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ባሉ የትምህርት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ጥናቶች በታሪክ ደረጃ ከመካከለኛው እና ከቅርብ ምሥራቅ ታሪክ (Near Eastern Studies) ተመድቦ መጠናቱ፤ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ከቀጣናው ጋር ያለውን ጥልቅ ታሪካዊ ውህደት የሚያረጋግጥ ሕያው ማሳያ ነው።
 
የባብ-ኤል-ማንደብ የባህር ወሽመጥ በጭራሽ መሰናክል አልነበረም፤ ይልቁንም ንግድን፣ ባህልን እና ማህበረሰቦችን በቀይ ባሕር በኩል ያገናኘ ዋንኛ መተላለፊያ ሆኖ አገልግሏል።
 
ከንጉሥ አብረሃ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝቦች መካከል የጋራ የደም ትስስር እንደነበር የሚያረጋግጡ ዘመናዊ የስነ ህይወት( ጄኔቲክስ) ጥናቶች፣ የዚህን ታሪካዊ ቁርኝት እውነተኛነት በግልጽ ያሳያሉ።
 
በቋንቋና በባህል ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረት ታሪካዊ ትስስር ያለው ነው። የሀገሪቱ የቋንቋና የሥነ-ጽሑፍ ውርስ ከዓረብኛ፣ አራማይክና ዕብራይስጥ ጋር በጽኑ የተሳሰረ ሲሆን፣ ይህም በምሥራቅ አፍሪካና በአረቢያ ልሳነ-ምድር መካከል ያለውን ጥልቅ የጋራ የሥልጣኔ ቁርኝት ያረጋግጣል።
 
ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላት። የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ወደ ኢትዮጵያ ተስደው በንጉስ ነጃሺ ከለላ ማግኘታቸው የእስልምናን ህልውና የታደገ ታሪካዊ ክስተት ሲሆን፣ ይህም ሀገሪቱን ከዓረቡ ዓለም ጋር በጽኑ አስተሳስሯታል።
 
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የዓረብ ሊግን በኢትዮጵያ ላይ እንደ ተቋማዊ ተፅዕኖ ማሳደሪያ መሣሪያ ግብጽ ስትጠቀምበት ቆይታለች። ግብፅ የውጭ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ዕድገት፣ የህዳሴውን ግድብም ሆነ የባሕር በር ጥያቄን እንደ ሥጋት በሚያይ ጊዜ ያለፈበት ስሌት ላይ የተመሠረተ ነው።  ግብፅ የራሷን የውሃ አቋም በሊጉ ላይ በመጫን፣ ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ አድርጋለች።
 
ጅብሪል ላሞ እንዳመለከተው፣ ከግብጽ የአግላይነት ፖሊሲ ይልቅ የዘመኑ ነባራዊ ሁኔታዎች ሙሉ ትብብርን የሚጠይቁ ናቸው። በመደመር መርህ፣ ኢትዮጵያ ለዓረቡ ዓለም ለዘመናት ከቆዩ የጥላቻ መንገዶች በላቀ ሁኔታ የተሻሉ ጥቅሞችን ማቅረብ ትችላለች።
 
እያደገ የመጣው የኢንዱስትሪ እና የአረንጓዴ ኃይል አቅሟ፣ ኢትዮጵያን ለቀይ ባህር ቀጣና የመረጋጋት  ምሰሶ አድርጓታል። የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና የውሃ እጥረት እና የምግብ ዋስትና ሥጋት በተጋረጠበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የውሃ ሀበት እና ለም መሬት ለቀጣናው ወሳኝ የግብርና-ኢንዱስትሪ አጋር ያደርጋታል።
 
የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ብሔረተኝነት በመሻገር፣ የቀይ ባህርን ቀጣና የሥልጣኔ እውነታ መቀበል ይኖርባቸዋል። አረብ ሊግ እንደ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኮሞሮስ እና ሞሪታኒያ አባል ሀገራት መያዙ፣ ስብስቡ የተለያዩ ቀጣናዊ እውነታዎችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑን ያሳያሉ።

የዓረብ ሊግ ሙሉ አባልነት የኢትዮጵያን አፍሪካዊ ማንነት ሳይቀንሰው፣ አህጉሩን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር የሚያገናኝ ዋነኛ ድልድይ የሚያደርጋት በመሆኑ፤ ሊጉ የኢትዮጵያን አጋርነት በመቀበል ለአዲስ አበባ ተገቢውንና ሕጋዊ ቦታዋን የሚሰጥበት ጊዜ አሁን እንደሆነ በመግለጽ ጅብሪል ላሞ ፅሁፉን ቋጭቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም