ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ጠንካራና አስተማማኝ ለማድረግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ውጤት እያመጡ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 13/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ጠንካራና አስተማማኝ ለማድረግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቴር ዳዊት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራ በስኬትና በውጤታማነት ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል።


 

የዲጂታል መሠረተ ልማቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከልና የሳይበር ሉዓላዊነትን የማስከበር ተግባርም በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል።

ይህንኑ ተግባራዊ ጥረት ለማጠናከርም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የወጣቶችን የሳይበር ደህንነት ክህሎት የሚያሳድጉ የክረምት ስልጠና ፕሮግራሞችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በተለይም የክረምት የስልጠና መርሃ-ግብር በሳይበር ደህንነት፣ በሶፍትዌር ልማት፣ በኮዲንግ እና በመረጃ ደህንነት ዙሪያ የተሻለ ክህሎት ያላቸውን ታዳጊና ወጣቶች በመሰልጠን ላይ ናቸው።

በዚሁ መሰረትም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በክረምቱ በአምስተኛ ዙር በርካታ ወጣቶችን የሳይበር ደህንነት ስልጠና በመስጠት ላይ ሲሆን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቴር ዳዊትና ሌሎች የመንግስት ስራ ኃላፊዎች በስፍራው በመገኘት ሰልጣኞችን አበረታትተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዚሁ መሰረትም የስልጠና እና ግንዛቤ ስራዎች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በክረምቱ ወላይታ ሶዶን ጨምሮ በስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ለወጣቶች ተመሳሳይ ስልጠና በመሰጠት ላይ መሆኑን አንስተው ይህም ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ጠንካራና አስተማማኝ ለማድረግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን አንስተው ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳይ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አክበር ጩፎ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመስጠት ብቁ ዜጎችን የማፍራት ስራውን መቀጠሉን ገልጸዋል።

ከቴክኖሎጂ፣ ከኢንዳስትሪና መሰል ተቋማት ጋር የመስራት ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው ይህም የተለየ ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች መልካም እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከሰልጣኞቹ መካከል ከዲላ ከተማ የመጣችው የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው መልካም አስራት እና ከሐዋሳ ከተማ የመጣችው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ኖሐሚን ንጋቱ፤ በስልጠናው ስለ የሳይበር ደህንነትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ ዕውቀት በመገብየት በዲጂታሉ ዓለም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረን አድርጎናል ብለዋል።

የወላይታ ሶዶ ነዋሪና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት  ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ፍሬው ቶማስ በበኩሉ ይህ ስልጠና ክህሎታቸውን ለማሳደግ አማራጭ ላጡ ወጣቶችና ተማሪዎች መልካም ዕድል መፍጠሩን ተናግሯል።


 

በስልጠናው የሳይበር ደህንነት እውቀት ማግኘቱን የጠቀሰው ወጣቱ  የመረጃ መንታፊዎችን በመዋጋት የሀገራችንን የመረጃ ደህንነት ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጧል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም