ቀጥታ፡

በ2019 ትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ደሴ፤ ነሐሴ 13/2018(ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማው ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2019 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በትምህርት ዘመኑ ከ77 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር እንቅስቃሴ ተጀምሯል። 


 

ለዚህም አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በየደረጃው የንቅናቄ መድረኮችን እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ከነገ ጀምሮም በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ እንደሚጀምር የተናገሩት ኃላፊው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምዝገባውን በማጠናቀቅ መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራው በይፋ ይጀመራል ብለዋል።

በትምህርት ዘመኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና ባለፉት ዓመታት የተጀመረውን የተማሪዎች ምገባ በማስፋፋት የትምህርት ጥራቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ለዚህም 20 አዳዲስ መማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለመማር ማስተማር ስራ ዝግጁ ከመሆናቸው ባለፈ፣ ነባር 128 መማሪያ ክፍሎች ደረጃቸው ተሻሽሎ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የመምህር አካለ ወልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አንዳርጌ አፍሬ በበኩላቸው፤ በ2019 ትምህርት ዘመን ከሁለት ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። 

ምዝገባውን በአምስት ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም የመማር ማስተማሩን ስራ ለመጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን  ተናግረዋል።

የ2019 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የሰኞ ገበያ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ረህመት ይመር ናቸው።

ለዚህም ግብዓት በማሟላት፣ ትምህርት ቤቱን የማሳመርና የማስዋብ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የከተማ፣ የክፍለ ከተማና የትምህርት ቤቶች አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም