በድሬደዋ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰማሩ አልሚዎችን በመደገፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰማሩ አልሚዎችን በመደገፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ማሳደግ ተችሏል
ድሬደዋ፤ ነሐሴ 13/2018(ኢዜአ)፦ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰማሩ አልሚዎችን በመደገፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ማሳደግ መቻሉን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ አመራር አካላት በሆቴል ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው ግንባታ ላይ የሚገኙ ባለኮከብ ሆቴሎችን የመስክ ጉብኝት አድርገዋል።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ የከተማዋን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት የቀየሰው የአሰራርና የህግ ማእቀፍ በርካታ አልሚዎችን ወደ ስራ ማስገባት አስችሏል።
ለዚህም የመሠረተ ልማት፣ የመሬት አቅርቦት፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የፋይናንስ እና ሌሎች ድጋፎችን ከመስጠት አኳያ ከተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህም በተለይም በሆቴሎች ዘርፍ ፈቃድ ወስደው በግንባታ ላይ የነበሩ አልሚዎች ስራቸውን አጠናቀው ወደ አገልግሎት በመግባት የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ እያሳደጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለአብነትም በበጀት አመቱ በግንባታ ላይ የነበሩ አምስት ሆቴሎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አንስተዋል።
ይህም ከተማዋን የቱሪዝም ኮንፍረንሰ ማእከል ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ለማሳካትና የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ማገዙን ገልጸዋል ።
የዛሬው ጉብኝትም አስተዳደሩ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለማበረታታት ያለመ ነው ብለዋል።
እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉ ሆቴሎችን በማበረታታት በፍጥነትና በጥራት ወደ አገልግሎት ለማስገባት አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን አባይ አስተዳደሩ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት የዘርፉን ጠቀሜታ ለማጉላት እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም መስህቦቹን ለጎብኚዎች አመቺ የማድረግና ከከተማዋ ኮሪደር ልማት ጋር ተሰናስሎ እንዲሄድ መደረጉን ገልጸዋል።
በከተማዋ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ፍሰትና የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ700 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ15 ሺህ በላይ ቱሪስቶች መስህቦቹን መጎብኘታቸውን አስረድተዋል።
የከተማዋ የቱሪዝም ልማትም የስራ እድልን ለማስፋትና የከተማውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ከፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በተያዘው በጀት አመትም በቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በግንባታ ላይ ከሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች ባለቤት አቶ ሱራፌል ሲሳይ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ስራቸውን ለማቀላጠፍ እያገዛቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በግባታ ላይ የሚገኘው ሆቴልም ለከተማዋ የቱሪስት ፍሰትና ለወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።