ቀጥታ፡

ህገ-ወጡ የህውሓት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፅመው ግፍና በደል ሊያበቃ ይገባል

ደብረ ብርሃን ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ ህገ-ወጡ የህውሓት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፅመው ግፍና በደል ሊያበቃ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው  የትግራይ ተወላጅ እናቶች ገለጹ።

ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን ከባንዳ እና ባዳዎች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ህዝቡን በማፈን በደሎችን እየፈጸመ ይገኛል።

በተለይም እናቶች እያለቀሱ ታዳጊዎች እና ህፃናትን በግዳጅ ወደ ውትድርና ከማሰማራት ባለፈ ለሱዳን አሳልፎ በመሸጥ ጥቅሙን እያግበሰበሰ ያለ የወንጀለኞች ስብስብ ሆኗል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ካነጋገራቸው የትግራይ ተወላጅ እናቶች መካከል ወይዘሮ ትርሐስ መዝገቡ እና ወይዘሮ ፀጋ ኪዳኑ፤ የህገ-ወጡ ህውሃት ቡድን ግፍና በደል እየበረታ ህዝቡ ለስቃይና እንግልት እየተዳረገ ይገኛል ብለዋል።

የህወሃት ቡድን የጥፋት ስብስብ ከህፃን እስከ አዋቂ በማፈንና በአስገዳጅነት ወደ ውትድርና በመውሰድ እናቶችን እያስለቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአረጀና በቆየ አስተሳሰብ እየተመራ ያለው ይህ ህገ-ወጥ ቡድን ለማንም የማይጠቅም የጥፋት ስብስብ መሆኑን ገልጸው የትግራይ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላምና ልማትን ይሻል ብለዋል።

በትግራይ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በመጣር ረገድ መንግስት ያደረገውን ተደጋጋሚ ጥረት ያደነቁት ወይዘሮ ትርሐስ፤ በክልሉ የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ ጭምር ህገ-ወጡ ህወሃት ምንም አይነት የሰላም ፍላጎት የሌለው መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

በመሆኑም የጥፋት ቡድኑ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፀመው ግፍና በደል እንዲያበቃ በጋራ መታገል ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ፀጋ ኪዳኑ፤ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት አካታችና ሁሉን አቀፍ ምክክር እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት ህገ-ወጡ ህወሃት “ጽምዶ” እያለ ለጦርነት የሚያደርገው ዝግጅት እና የሀገር ክህደት ቡድኑ መቼም ቢሆን ሰላም ፈላጊ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በጦርነት አዙሪት እድሜውን በማራዘም ከክልሉም ባለፈ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን በግልጽ ማሳወቁን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይም የትግራይ ክልል ህዝብ ሊታገለውና በህግም ተጠያቂ ልናደርገው ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም