ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የአፈር ለምነትን የሚያሻሽል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ የአፈር ለምነትን የሚያሻሽል 86 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የአፈር ለምነት ባለሙያ አቶ አምሳሉ አድማስ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሲድ የተጠቃ አፈር ለምነትን ለመመለስና የሰብል ምርታማትን ለማሳደግ የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘጋጅቶ መጠቀም ጠቀሜታው የጎላ ነው።


 

ለዚህም በበጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮችን በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በማሳተፍ 86 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ግብ ተይዞ ወደተግባር ተገብቷል።

ከቅጠላቅጠሎች፣ ከተረፈ ምርት፣ ከከብቶች እዳሪ፣ ከአመድና ለኮምፖስት ዝግጅት ጠቃሚ ከሆኑ ሌሎች ንጥረ ነገሮች ጥራቱን ጠብቆ እንዲዘጋጅ ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሳይንሳዊ ሂደቱን ጠብቆ ከተዘጋጀ የአፈር ቅንጣትና ለምነት እንዲሻሻል፣ የሰብል ምርታማነት እንዲጨምር፣ አፈር በውስጡ ውሃን ለረጅም ጊዜ እንዲቋጥር የጎላ ጠቀሜታው እንዳለውም አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለቀጣይ ዓመት መስኖና የመኽር እርሻ ጥቅም ላይ ለማዋል ከወዲሁ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በማዳበሪያ ዝግጅቱ እየተሳተፉ ካሉት መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታደሰ አለሙ በሰጡት አስተያየት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀትና መጠቀም ከጀመሩ ከ15 ዓመት በላይ እንደሆናቸው ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ላይ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት የካበተ ልምድና ዕውቀት በዓመት እስከ 23 ሜትር ኩብ ኮምፖስት ማዳበሪያ በጥራት አዘጋጅተው እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

የሚያዘጋጁትን ኮምፖስት ማሳቸው ላይ በመጨመር የአፈር ለምነትን ከማሻሻል ባለፈ የሰብል ምርታማነትና ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን አመልክተዋል። 

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ለምነቱን አጥቶ ከምርት ውጭ ሆኖ የቆየ ግማሽ ሄክታር መሬት ለምነቱ መመለሱን የገለጹት ደግሞ በዞኑ የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር ፈጠነ አስረስ ናቸው።

ከዚህም በየዓመቱ እስከ 12 ኩንታል የስንዴና የገብስ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተያዘው በጀት ዓመትም 18 ሜትር ኩብ ኮምፖስት በጥራት አዘጋጅተው ለመጠቀም ወደሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል። 

የቢሮው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተዘጋጀ ከ81 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመስኖና ለመኸር ሰብል ልማት ጥቅም ላይ መዋሉ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም