ቀጥታ፡

መደመር የደረመሠው የጠላት ካምፕና የባንዳዎች እሪታ

በምስራቅ አፍሪካና በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የካይሮ እጅ ሁልጊዜም ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉ እኩይ ስትራቴጂዎችን በመተለም ይታወቃል። የዓባይ ወንዝ ዋነኛ ምንጭና የተፈጥሮ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ማዳከም፣ የውስጥ ግጭቶችን ማበረታት እና በቀይ ባሕር እንዲሁም በኤደን ባሕረ-ሰላጤ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ፍላጎት ማደናቀፍ የግብፅ የረጅም ጊዜ የውጭ ፖሊሲ መሠረት ሆኖ ቆይቷል።

ግብፅ 19ኛው ክፍለ ዘመን በወታደራዊ ኃይል ኢትዮጵያን በግልጽ ወርራ ለመቆጣጠር ባደረገችው ሙከራ  እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1875 በጉንደት እንዲሁም  1876  በጉራዕ  ጦርነቶች በኢትዮጵያ አሳፋሪ ሽንፈት አስተናግዳለች ። ከዚህ የቀጥታ ወታደራዊ ሽንፈት በኋላ ካይሮ ኢትዮጵያን በግልጽ ጦርነት ማንበርከክ እንደማትችል ተረድታ ወደ ተዘዋዋሪ የውስጥ ሴራና የእጅ-አዙር ጦርነት ተሸጋግራለች።

ካይሮ ኢትዮጵያ ጠንካራና የበለፀገች ሀገር ሆና ከተነሳች በዓባይ ውሃ ላይ ያላትን አጠቃላይ የበላይነት እንደምታጣ ስለሚሰማት፣ የሀገሪቱን እድገት የማደናቀፍና በጂኦፖለቲካው መስክ ወደብ አልባ አድርጎ የመዝጋት ስትራቴጂን ለዘመናት ስትከተል ኖራለች። ይህም  የታሪክ እውነታ ከትላንት እስከ ዛሬ በስውርና በግልጽ የሴራ መረቦች ተሸርቦ የኢትዮጵያን  ብሔራዊ ጥቅም ሲፈታተን የኖረ መራራ እውነት ነው።

የቡትሮስ  ብትሮስ ጋሊ የዲፕሎማሲ ሽፋን እና ኢትዮጵያን ወደብ የማሳጣት ሴራ

በታሪክ አጋጣሚዎች እንደምናየው፣ በግብፅ የፖለቲካ ልሂቃን የታቀዱ ሴራዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዴት ተግባራዊ እንደሆኑ አንደኛው ማሳያ የቀድሞው ግብፃዊ ዲፕሎማት ቡትሮስ ቡትሮስ-ጋሊ አካሄድ ነው። ቡትሮስ-ጋሊ 1970ዎቹ መጨረሻ በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራር በነበሩበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ በውስጥ ግጭት እንድትታመስና የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ስጋት እንዳትሆን ከበስተጀርባ የዓመፅ ኃይሎችን የማጠናከር ስራ ሲሰሩ እንደነበር የሚታወቅ ሃቅ ነው።

ቡትሮስ-ጋሊ በውሃ ፖለቲካ ረገድ በሰጡት የታወቀ ንግግራቸውቀጣዩ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና የሚካሄደው ጦርነት በፖለቲካ ምክንያት ሳይሆን በውሃ ምክንያት የሚደረግ ይሆናል በማለት  ለቀጣናው ያሰቡ መስለው የካይሮን የውሃ የበላይነት ስጋትና ፍላጎት በግልጽ አንጸባርቀው ነበር። ይህ ንግግራቸው ግብፅ የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት የመቆጣጠር ፍላጎቷንና ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዳታካሂድ ለማድረግ የምታደርገው ሴራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ  ዓላማ ያደረገ አደገኛ ንግግር ነው።

በኋላም .. 1993 ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመገንጠል ሂደት ውስጥ ቡትሮስ ቡትሮስ-ጋሊ የስድስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ ነበሩ። በወቅቱ 99 ነጥብ 8% የሚሆኑት ኤርትራዊያን በሕዝበ ውሳኔ ነጻ ሀገርንትን መርጠዋል በሚል ሕወሃትና ሻዕቢያ የሰሩት ድራማ ተቀባይነት አንዲያገኝ የተመድ ዋና ጸሐፊው ከፍተኛ ሴራ ሰርተዋል። ይህ የኤርትራ ህዝብን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በሻዕቢያ ባርነትና ግዞት እንዲማቅቅ ያደረገው የሕዝበ ውሳኔ ድራማ ላይ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የመሪ ተዋናይነትን ሚና ተጫውተዋል። በሂደቱም ዋነኛ ዓላማቸው የሆነውን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር በሯን እንድታጣ አድርገዋል። ይህም የካይሮ የረጅም ጊዜኢትዮጵያን የመዝጋትስትራቴጂ አካል እንደነበር ግልጽ ነው።

የካይሮ መጥረቢያ እና አሁናዊው የጥፋት መንገድ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት የመጥረቢያ ተምሳሌታዊ ማብራሪያ፣  ሕገ ወጡ ሕወሃትን እንደ መጥረቢያ ብረት፤ ሻዕቢያን  ደግሞ እንደ መጥረቢያ ዛቢያ ያስቀመጡ ሲሆን፤ መጥረቢያውን የሚያዘውና የሚወረውረው ሌላ ሶስተኛ አካል መኖሩንም ተናግረዋል።

እንደሚታወቀው መጥረቢያ አንድን ነገር የመቁረጥና የማፍረስ ስራ ለማከናወን የሶስት አካላት ቅንጅት ያስፈልገዋል፦ ወርዋሪው (እጁ) ዛቢያው (መያዣው) እና ብረቱ (ቁራጩ) በዚህ ተምሳሌት ውስጥ ወርዋሪው ወይም መጥረቢያውን ጨብጦ ስራ ላይ የሚያውለው አካል ግብፅ ናት። ወርዋሪው ሁልጊዜም ከበስተጀርባ ሆኖ ስትራቴጂ ይነድፋል፣ ፋይናንስና ወታደራዊ ድጋፍ ያቀርባል፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሽፋን ይሰጣል። በሌላ በኩል የመጥረቢያ ብረት ያለ ዛቢያው (መያዣው) ኃይል አግኝቶ ማረፍ አይችልም፤ ዛቢያውም ያለ ወርዋሪው እጅ መንቀሳቀስ አይችልም። በዚህ ሂደት ሻዕቢያ (እንደ ዛቢያ) በቀጣናው ውስጥ የካይሮን ፍላጎት ለማስፈጸም የመያዣነት  ሚና ይጫወታል። ቀጣናውን ለማተራመስ በሞመከር የካይሮን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ለማሳካት መንገድ ይከፍታል። ህገ-ወጡ ህወሓት  ደግሞ እንደ መጥረቢያ ብረት በሀገር ውስጥ ሆኖ የሀገሪቱን መዋቅር፣ የህዝቦችን አንድነት እና ስትራቴጂካዊ ብሔራዊ ጥቅም ለመሸርሸር የሚሰራ ተላላኪ መሳሪያ ነው።  በዚህ የሴራ ትስስር አሁን ላይ ኢትዮጵያ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ማደናቀፍ ዋነኛ ዓላማው አድርጎም እየሰራ ይገኛል። 

ግብፅየቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ-ሰላጤ የባሕር ወሰን ያላቸው ሀገራት ብቻ ናቸው  በውሃው ላይ መወሰን ያለባቸው”  የሚል መርህ በማንሳት፣ 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትንና በቀይ ባሕር ዳርቻ  የሚገኘውን ትልቁን ኢኮኖሚ (ኢትዮጵያን) ያገለለ ህገ-ወጥ ስብስብ ለመፍጠር እየሰራች ነው።

በተጨማሪም በቅርቡ ከሶማሊያና ከሌሎች የአካባቢው ሀገራት ጋር የተደረጉ የውትድርናና የደህንነት ስምምነቶች፣ የሶማሊያን ሰላም ለማስጠበቅ ሳይሆን ቀጣናውን ለማተራመስና ወታደራዊ ስጋት ለመፍጠር የተቃኙ ናቸው። ይህ ሁሉ አካሄድ ዋነኛ ዓላማው ቀጣናውን የውክልና ጦርነት ማዕከል በማድረግና ኢትዮጵያ ወደ ባሕር እንዳትቀርብ ሆነ ተብሎ የተሰላ ሴራ ነው። ከቡትሮስ ቡትሮስ-ጋሊ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ እስከ ዛሬው የቀይ ባሕር ሴራዎች ድረስ የተዘረጉት መረቦችም ይህንኑ እውነት ያሳያሉ።

የካይሮ መጥረቢያዎችን ያዶለዶመው የመደመር መንግሥት ጥንካሬ

ግብጽ እያከናወነችው ባለው አሁናዊ ሴራ ውስጥ የካይሮ ስትራቴጂስቶች የሳቱት ትልቅ እውነታ አለ። የግብጽ የሴራ መጥረቢያዎች ለመቁረጥ  የሚሞክሩት በፈተናዎች የማትበገረውን እና እንደ ወርቅ በእሳት ውስጥ ተፈትና ያለፈችውን ኢትዮጵያን መሆኑ ነው።  ኢትዮጵያ በታሪኳ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎችን አሸንፎ መውጣት እንግዳ የሆነባት ሀገር አይደለችም። ባለፉት ክፍለ ዘመናት በወረራ፣ በውስጥ አለመረጋጋትና በጂኦፖለቲካዊ ከበባዎች ውስጥ አልፋ የጸናች ሀገር ናት። ወርቅ በእሳት ውስጥ ሲያልፍ ቆሻሻው ተወግዶ ይበልጥ እንደሚበራ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በተጋረጡባት የህልውና ፈተናዎች ሁሉ  አልፋ ይበልጥ እየጠነከረችና እየተደራጀች መምጣቷ የታሪክ እውነታ ነው።

አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ይህ ጥንካሬዋ ይበልጥ ጎልብቷል።  የመደመር መንግሥት ቁልፍ ፍልስፍና እናየተገበራቸው ያሉ  እርምጃዎች የካይሮን የረጅም ጊዜ የእጅ አዙር ጦርነትና ሴራዎችን ከንቱ ያደረገ ነው

የመደመር መንግሥት የውጭ ጫናዎችንና ሴራዎችን ለመመከት የመጀመሪያው ምሽግ የውስጥ አቅምን ማጠናከር መሆኑን በመገንዘብ፣ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለፍፃሜ ማብቃትና ግዙፍ የግብርና፣ የአረንጓዴ አሻራ እና የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን እውን አድርጓል። ይህም ግብፅ ኢትዮጵያን በልማት እንዳትበለፅግ ለማድረግ ያቀደችውን ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ አክሽፎታል።

ካይሮ ኢትዮጵያን በጂኦፖለቲካዊ ከበባ ለማዳከምና በውስጥ ልዩነቶች ላይ እሳት በማንደድ ሀገሪቱን ለማፍረስ የነደፈችው የረጅም ጊዜ የሴራ መረብ፣ የመደመር መንግሥት ባስመዘገባቸው የልማትና የዲፕሎማሲ ድሎች ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተደርምሷል። ይህ የጠላት ካምፕ መደርመስና የኪሳራ ስሌት ደግሞ በካይሮ ስትራቴጂስቶችና በውስጥ ተላላኪዎቻቸው (ባንዳዎች) ዘንድ ታላቅ ድንጋጤንና ተስፋ የመቁረጥ እሪታን ፈጥሯል። በመሆኑም የተበተነው የጠላት ካምፕና የተበሳጩት ባንዳዎች ብቸኛ አማራጭ አድርገው የያዙት በሳይበርና በሚዲያ ምህዳር የሃሰት መረጃዎችን ማንደድና የፕሮፓጋንዳ ማዕበል መፍጠር ቢሆንም፣ ይህም የተስፋ መቁረጥ ድምፅ ብክለት እንጂ የኢትዮጵያን የጽናት ጉዞ የሚያስተጓጉል አይሆንም።

በሌላ በኩል ግብፅየቀይ ባሕር ሀገራት ጥምረትበሚል ስም ቀጣናውን ለማተራመስና እርስ በርስ ጥርጣሬ ለመፍጠር የምታደርገውን የሴራ መረብ፣ የመደመር መንግሥት የጋራ እድገትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በማስቀደም በዲፕሎማሲው መስክ እየመከተው  ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ ምክክር የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በጋራ እንዲወስኑ በማድርግም  የካይሮ ስትራቴጂስቶች በኢትዮጵያ የውስጥ ልዩነቶች ላይ እሳት በማንደድ ሀገሪቱን ለማፍረስ የጠነሰሱትን ሴራ ከንቱ አድርጎታል።

በአጠቃላይ ታሪክ እንደሚነግረንና የወቅቱ እውነታ እንደሚመሰክረው፣ የግብፅ የሴራ መጥረቢያዎች በፈተናዎች እሳት ተፈትና ባላለፈች ደካማ ሀገር ላይ ያረፉ አይደሉም። ለመቁረጥ የሞከሩት በጽናት፣ በህዝቦቿ መስዋዕትነትና በፅኑ ታሪካዊ መሰረት ላይ የቆመችውን ኢትዮጵያን ነው።

አሁን ላይ በመደመር መንግሥት መሪነት እየተገነባ ያለው የውስጥ አቅም፣ የልማት ስኬትና በራስ መተማመን የካይሮን የረጅም ጊዜ የከበባ ሴራ ሙሉ በሙሉ ወድቅ ማድረጉን ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ሁሉ አሸንፎ ማለፍ የሰርክ ተግባሯ እንደመሆኑ መጠን፣ የዛሬውንም የጂኦፖለቲካ ውጥረትና የሴራ መረብ በጽናት አልፋ የቀጣናው የልማትና የሰላም ማዕከል ሆና መቀጠሏ የማይቀየር እውነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም