የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ከ120 ሺህ ለሚበልጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ከ120 ሺህ ለሚበልጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ
ዲላ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፡-የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታሉ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ነጻ የሕክም እየሰጠ ነው።
በተያዘው ክረምትም የዲላ ማረሚያ ተቋምን ጨምሮ በከተማዋ በአራት ጊዜያዊ ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ የነጻ የሕክም አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
የሕክምና አገልግሎቱ የሳንባ ነቀርሳና የስነ አዕምሮ ጤና ዘርፎችን ጨምሮ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ልየታ፣ ሕክምናና የመድሃኒት አቅርቦትን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ከ120ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ በበጎ ፍቃድ የሕክምና አገልግሎቱ ስፔሻሊስት ሃኪሞችን ጨምሮ 100 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ከነጻ የሕክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የደም ልገሳና የአረጋዊያን ድጋፍ መርሀግብሮች መከናወናቸውን ጠቁመው፣ የተሰጠው ነጻ የሕክምና አገልግሎት የሆስፒታሉን ጫና አቃሎታል ብለዋል።
በቀጣይም ነጻ የሕክምና አገልግሎቱ ከከተማው ወጭ በጌዴኦ ዞን እና አጎራባች ወረዳዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በማረሚያ ተቋሙ የተሰጠው ነጻ የሕክምና አገልግሎት የታራሚዎችን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር ትልቅ የሞራል ድጋፍ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ማረሚያ ተቋም አዛዥ ኢንስፔክተር ትዕግስት ሮቤ ናቸው።
የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራሮች እና የጤና ባለሙያዎች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ነጻ የሕክምና አገልግሎት ካገኙት ነዋሪዎች ውስጥ አቶ ታፈሰ ፎላ በነጻ ሕክምናው ሙሉ የጤና ምርመራ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በምርመራውም የወባ በሽታ እንዳለባቸው ምልከት በመታየቱ በሆስፒታሉ የመድሃኒት አገልገሎትም ማግኝታቸውን ተናግረዋል።
ነጻ የሕክምና አገልግሎቱ ሙሉ የጤና ሁኔታቸውን ለማወቅ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ድግሞ ወይዘሮ እቴነሽ ወርቁ ናቸው።
በተለይ የዓይንና የስነ አዕምሮ ምርመራ በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለተሰጣቸው ነጻ የምርምራ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።