ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የምታከናውነውን ጥረት ኖርዌይ ትደግፋለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ ኖርዌይ ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የምታከናውነውን ጥረት በቁርጠኝነት እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ የደንና አየር ንብረት ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛና አማካሪ ላይቭ ጃኮብ ሲድነስ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመከላከል በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ልማትና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለቀጣናው ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ተግባር በማከናወን ላይ ትገኛለች።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ የደንና አየር ንብረት ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛና አማካሪ ላይቭ ጃኮብ ሲድነስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በደን ልማት ዘርፍ አስደናቂ ለውጥ ተገኝቷል፡፡


 

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርና በአፈርና ውሃ ጥበቃ በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት በሀገሪቱ የደን ሽፋን ላይ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

ኖርዌይ ባለፉት አስርት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የደን ሽፋን ማሳደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ አድርገናል ብለዋል፡፡

የደን ልማት የአፈር መሸርሸርን መከላከልና የአፈርና ውሃ ሀብት ጥበቃ በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በቀጣናው የውኃ አቅርቦትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

ኖርዌይ ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የምታከናውነውን ጥረት በቁርጠኝነት እንደምትደግፍም ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት በደን ጥበቃ ስራዎች በመተባበር የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ እንደሚሰሩ ጠቅሰው፤ ኖርዌይ የኢትዮጵያ የሬድ ፕላስ መርሃ ግብር ትግበራ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የተነደፈውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ለመደገፍ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም