ቀጥታ፡

በዞኖች ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ሆሳዕና ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤታማ መሆኑን የጉራጌ፣ ስልጤና ከምባታ ዞኖች አስታወቁ።

በስልጤ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ሁሴን እንዳሉት፣ በዞኑ የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ባለው ጥረት ውጤት ተመዝግቧል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍን ለመሸፈን የሚውል የእህል ክምችት ለመያዝ በተከናወነ ተግባር፣ እስከ አሁን ከ11 ሺሕ 860 ኩንታል በላይ ምርት በወል መሬት ላይ አምርቶ ማከማቸት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማህበረሰቡን በማሳተፍ 22 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ማከማቸት ተችሏል ብለዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም በዞኑ በመኸር ወቅት 207 ሄክታር ማሳ በበቆሎ ሰብል ለዚሁ ተግባር እየለማ እንደሚገኝ አመልክተዋል። 

በተጨማሪም 30 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጊዜወርቅ አለሙ በበኩላቸው፣ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በማህበረሰብ ተሳትፎ 6 ሺሕ 800 ኩንታል እህል ማከማቸት ተችሏል ብለዋል። 

በተያዘው የበጀት ዓመትም በዞኑ በመኸር ወቅት 260 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲሆን ፣ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የመጠባበቂያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ግብ ተጥሎ ወደ ትግበራ መገባቱን አመልክተዋል።


 

በከምባታ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ማቲዎስ እንደገለጹት ደግሞ፣ በዞኑ በተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻል ከማህበረሰቡ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል። 

በዚህም 480 ኩንታል የምግብ እህል ከማምረት ባሻገር፣ 22 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል። 

በመኸር እርሻም 180 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ሲሆን 124 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም