ቀጥታ፡

የሻደይ በዓል የሀገር ባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ ገበያን እያነቃቃ ነው - የባህል ልብስ ሰሪና አቅራቢዎች

ሰቆጣ፤ ነሃሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በየዓመቱ የሚከበረው የሻደይ በዓል የአካባቢውን ባህልና ትውፊት ከማስተዋወቅ ባለፈ የሀገር ባህል አልባሳትና የጌጣጌጥ ገበያን እያነቃቃ እንደሚገኝ ነጋዴዎች ገለጹ።

የልጃገረዶች ጨዋታና የውበት መግለጫ፣ የባህል አልባሳትና የጌጣጌጥ ድምቀት የሆነው የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል የዓመቱ ማጠቃለያና የአዲሱ ተስፋ ማብሰሪያ በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ይከበራል።

የሴቶችን ማህበራዊና ባህላዊ እሴት ከማጎልበት ባለፈ የአገር ባህል አልባሳት፣ የጌጣጌጥና የቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚያነቃቃው የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በየዓመቱ ከነሐሴ 15 ቀን ጀምሮ በስፋት ይከበራል።


 

የሻደይ በዓል ሴቶች በአቅማቸው ልክ የባህል አልባሳትንና ጌጣጌጥ በመግዛት አጊጠውና ተውበው ለማክበር ዕለቱን በናፍቆት የሚጠብቁት ዓመታዊ በዓል ነው።

በሰቆጣ ከተማ የባህል አልባሳት ነጋዴ የሆኑት ወይዘሮ አበበች ወርቁ፤ ለበዓሉ የዋግ ባህል መገለጫ የሆኑ አልባሳትን አዘጋጅተው እየሸጡ መሆኑን ገልፀዋል።

በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ የአካባቢው ማሕበረሰብ የባህል አልባሳትን በማዘጋጀት ይዘው መቅረባቸውን ጠቁመው፣ በዓሉ ሲደርስ ገበያው የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መዝገቡ ሚሰነ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ ለባህል አልባሳት እየሰጠ ያለው ትኩረት በገበያው ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ በመሆኑ በዘርፉ ለመሰማራት አስችሎኛል ነው ያሉት ።

የአካባቢው ማህበረሰብም ከጊዜ ወደ ጊዜ የባሕል ልብሱን ከመሸመን ጀምሮ በጥልፍና በስፌት ሥራ በመሰማራት ተጠቃሚነቱን እያሳደገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በመጪው ነሐሴ 15 ጀምሮ ለሚከበረው የሻደይ በዓል የሚሆን በቂ የባህል አልባሳትን አዘጋጅተው ማቅረባቸውን ያመለከቱት አቶ መዝገቡ፣ ህብረተሰቡም ገበያዉን እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርጋ ማርዬ እንዳሉት፤ የዘንድሮው የሻደይ በዓል "ሻደይን እናከብራለን፤ እሴቶቻችንን እንጠብቃለን" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

መምሪያው በዓሉ ባህላዊ ክዋኔውንና እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየሰራ ሲሆን፣ ለዚህም የባህል አልባሳት ሰሪዎች፣ በጥልፍ ሥራ የተሰማሩና አቅራቢዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

ከነሐሴ 15 ጀምሮ ለሚከበረው የሻደይ በዓል እሴቱንና ትውፊቱን የጠበቀ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ እንዲቀርብ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱንም አስረድተዋል።

በዓሉ በየአካባቢው የተለያየ መጠሪያ ስም ያለው ሲሆን፣ ሻደይ በዋግ ኽምራ፣ አሸንድዬ በላስታ/ወሎ፣ ሶለል ደግሞ በራያ ተብሎ እንደሚሰየም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም