ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ምርቶቿን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ የወጪ ንግድ አቅሟን እያሳደገች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ምርቶቿን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ የወጪ ንግድ አቅሟን እያሳደገች መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢትዮጵያና የቻይናን ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ላቀ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር የሚያሸጋግረውና የፕሮሞሽን ሥራዎች አካል የሆነ "Export to China" መድረክ በይፋ ተጀምሯል።


 

በመድረኩ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ፣ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አስመጪና ላኪዎች ታድመዋል።

በመድረኩ የቻይና አስመጪዎች ጥራት ያላቸውን የኢትዮጵያ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት እንዲገዙ ለማድረግ የሚያስችል የፕሮሞሽን ሥራዎች ተከናውኗል።

በዚህም ከ340 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው 33 የንግድ ለንግድ (B2B) የግብይት ኮንትራቶች በቡና፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ በጨርቃጨርቅ እና በማዕድን ዘርፎች ወደ ውጭ ለመላክ ተፈራርመዋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የስምምነቱ ዓላማ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ ግኝት ለማሳደግ የሚያስችል የፕሮሞሽን ሥራዎችን በቻይና ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ከቻይና ኤምባሲ ጋር ሰፋፊ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ ስምምነቱ ከብዙ ሥራዎች በኋላ የተገኘ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

33 የሚጠጉ ስምምነቶች መፈረማቸውን ገልጸው፤ እነኝህም 340 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል። ስምምነቱን ወደ ትልቁ የቻይና ገበያ ለመግባት በቻይና መንግሥት የተቀረጸው ኢኒሼቲቭ አካል መሆኑን አንስተዋል።

በቡና፣ በቅባት እህል፣ በጥራጥሬ፣ በቆዳ፣ በማዕድን ምርቶች እና በጨርቃ ጨርቅ ላይ ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

ስምምነቱ ከቃል በዘለለ ተግባራዊ ውጤት የተገኘበት ስኬት መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግሥት በ2019 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ማቀዱን ገልጸው፤ ስምምነቱ ይህንን ማሳካት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ የሚያስተዋውቅና ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ የተያዘውን ውጥን የሚያሳካ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣዮቹ ጊዜያትም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ምርቶችን በጥራት በዋጋ እና በብዛት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጠሉም እንዲሁ።


 

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው የስምምነቱ ዓላማ ለሁሉም የወጪ ንግድ ትልቅ ገበያ ማግኘት መሆኑን ገልጸዋል።

ቻይና በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ እጅግ አያሌ ምርቶችና የበለጸጉ ተፈጥሯዊ ሀብቶችም እንዲሁ በፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሁለቱ ገበያዎች እና ምርቶች መካከል ያለው ትስስር የሀገራቱን እድገት ለማፋጠን አስፈላጊ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

ስምምነቱ ቻይና ከአፍሪካ እና ከኢትዮጵያ ጋር የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ከተቀበለች እና መተግበር ከጀመረች ወዲህ የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም