በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመኸር እርሻ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል- መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመኸር እርሻ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል- መምሪያው
ደሴ፤ነሐሴ 13/2018( ኢዜአ):-በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በመኸር ወቅት የሚከናወነው የአረምና ተባይ ቁጥጥር ሥራን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በያዝነው መኸር በኩታ ገጠምና በመስመር በመዝራት እንዲሁም ግብአትን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም በ58 ሺህ 632 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራውን የሰብል ቡቃያ የአረምና የተባይ ቁጥጥር ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።
የተዘራውን ሰብል እስከ ሁለት ጊዜ በማረም ነጻ የማድረግና በየቀኑ ማሳውን በማሰስ ተባይን በመቆጣጠር ምርታማነቱን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያና ኢንዱስትሪ ግብአት ለማቅረብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የዝናብ መቆራረጥ ለመቋቋም አርሶ አደሩ በማሳው ዳርና ዳር ጉድጓዶችን በመቆፈር ውሃ የማሰባሰብ ስራ እንዲያከናውን ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
በአርጠማ ፉርሲ ወረዳ የዲምቱ ጨቆርሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ ከድር በሰጡት አስተያየት፣ በዘንድሮው መኸር ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በማሽላ፣ ማሾና በሌሎችም ሰብሎች አልምተዋል።
ሰብሉን ከአረም በማጽዳትና በየቀኑ የተባይ ቁጥጥርና አሰሳ በማካሔድ ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አልመው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላው የዳዋጨፋ ወረዳ የሸክላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አደም በበኩላቸው፣ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ በመታገዝ ፈጥነው የሚደርሱና ምርታማ የሆኑ ሰብሎችን ማልማት መቻላቸውን ገልጸዋል።
አንድ ሄክታር መሬታቸውን ማሽላና ጤፍ በኩታ ገጠም ማልማታቸውን ጠቁመው፣ የዝናብ መቆራረጡን ለመቋቋም ውሃ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ በመኸር ከለማው መሬት ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።