ቀጥታ፡

ምክክሩ ኢትዮጵያን ማጽናት የሚያስችል ትልቅ መሰረት እየጣለ ይገኛል-ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ) ፦ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን በጠንካራ የተግባቦት ዓለት ላይ ለማጽናት ትልቅ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ለዘመናት በኢትዮጵያ የዘለቁ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት፣ኢትዮጵያዊያን ካለፈው ኋላቀር እሳቤ በመላቀቅ ሁሉንም ያሳተፈ ምክክር እያደረጉ ይገኛል።

ይህ ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን እየተመካከሩበት በሚገኘው በዚህ ጉባኤ፣የተመካካሪዎች ሀሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርበት ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ አውድ ተፈጥሯል።

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን በጠንካራ የተግባቦት ዓለት ላይ ለማጽናት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ተመካካሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከተመካካሪዎች መካከል የአፋር ነጻ አውጪ ግንባርን ወክለው የመጡት ሀጂ እስማኤል መሀመድ እንዳሉት፣የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማካተት በሰለጠነ አግባብ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩ ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት በመሆኑ ዘላቂ ሰላም እና ሀገራዊ መግባባትን ለማስፈን ትልቅ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወክለው የሚወያዩበት ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ የሀገሪቱን የልማት እና የዴሞክራሲ ጉዞ ለማቀላጠፍም ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተናግረዋል።


 

ሌላኛው ተመካካሪ የሲዳማ አርነት ንቅናቄን ወክለው በመሳተፍ ላይ ያሉት ደምሴ ስኳሬ ፣ የምክክር ሂደቱ ከመነሻው ጀምሮ ግልጽነትና አሳታፊነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሂደቱ ከታች ጀምሮ የተለያዩ ሀሳቦችን በማብሰልና በማዋሃድ ወደ ላቀ የጋራ ሀገራዊ መግባባት የሚያደርስ እና ይህም የሂደቱን የሰለጠነ አካሄድ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ምክክሩ ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የመላው ተመካካሪዎች ድምፅ በነጻነት የተደመጠበት ሁሉን አቀፍ ጉባኤ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን በመወከል በመሳተፍ ላይ ያሉት ተመካካሪ ነጻነት ጣሰው ናቸው።


 

ተመካካሪዎች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁና ጠንካራ አዎንታዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ሰፊ ዕድል በመፍጠር ሂደት ውስጥ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ ገንቢ ሀሳቦች እየተነሱበት በመሆኑ የመደማመጥ እና የጋራ መግባባት ባህልን ለማጠናከር ትልቅ አጋጣሚ መፈጠሩንም አንስተዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መካተታቸው የተሻለች ሀገር በጋራ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም