ቀጥታ፡

ከምክክር ጉባዔው ለፖለቲካዊ አለመግባባቶች መፍትሔ የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን እንጠብቃለን - የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች

አዳማ፤ ነሐሴ 13/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለፖለቲካዊ አለመግባባቶች መፍትሔ የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን ይሰጣል የሚል ትልቅ እምነት እንዳላቸው የአዳማ ከተማ አባ ገዳ እና የሃይማኖት አባት ተናገሩ።

ከሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የአዳማ ከተማ አባ ገዳ እና የሃይማኖት አባት፣ አካታችነቱና አሳታፊነቱ ጎልቶ የታየው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው በፖለቲካዊ አለመግባባቶች ላይ ዘላቂ መፍትሔና ምክረ ሃሳቦችን ያመጣል የሚል ትልቅ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ የቦኩ ክፍለ ከተማ አባገዳ ተሾመ ስማ እንደገለፁት ሀገራዊ ምክክሩ በዘመናት ውስጥ ሀገራችን ያገኘችው ታሪካዊ ድል ነው ብለዋል።

ተመካካሪዎች ህዝቡን ወክለው ለኢትዮጵያ የተሻለ መፍትሔ ለማስቀመጥ እየመከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ በሀገሪቱ በህዝቦች መካከል የቆዩ ቅሬታዎችንና ቁርሾዎችን በመሻር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ትልቅ መሰረት እንደሚጥል ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር ጉባዔውን ምክረ ሀሳቦች በማክበርና ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ መተባበር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሀገራችንና ህዝባችን ይህንን እድል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አባገዳው፤ ከምክክር ጉባዔው ትልቅ ውጤት እንደሚጠብቁም አክለው ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባል ሼህ አብዱልቃድር አህመድ እንደገለፁት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የነበሩ ቁርሾዎችን በሁለንተናዊ መልኩ እንደሚፈታ ተስፋ አድርገዋል።

በተለይም በሀገሪቱ የነበሩትን የፖለቲካ አለመግባባቶች ለመቅረፍ ብቸኛው መፍትሔ ምክክር መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክሩ ጥሩ መፍትሔ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የገለጹት ሼህ አብዱልቃድር፤ ለተፈጻሚነቱ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የቀድሞ ታጣቂዎች፣ የሃይማኖት ተወካዮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የፀጥታ አካላት እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የምክክር ጉባዔ በመሆኑን ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ አጀንዳ ከማሰባሰብ ጀምሮ ሁሉንም ያማከለ፣ አሳታፊና አካታች እንደነበር የገለጹት ሼህ አብዱልቃድር፤ ሂደቱ ለሀገራችን ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያመጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም