ቀጥታ፡

በምክክር ጉባኤው ምክረ ሀሳቦች የተጠናቀረው የመጨረሻ ሰነድ ነገ ለአራት ሺህ ተመካካሪዎች በጋራ ይቀርባል-ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ላይ የተጠናቀረው የመጨረሻ ሰነድ ነገ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ለአራት ሺህ ተመካካሪዎች በጋራ እንደሚቀርብ አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አሁናዊ ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ከስምንቱም ቡድኖች የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ለማጣጣም የተቋቋመው 120 አባላት ያሉት አጠናቃሪ ቡድን በጥንቃቄ ሲሰራ ቆይቶ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ አንድ ወጥ የሆነ ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፣ የተዘጋጀው ሰነድ ዛሬ ጠዋት ለየስምንቱ ቡድኖች የቀረበ ሲሆን፣ ቡድኖቹ ሰነዱን አዳምጠው የመጨረሻ ግብዓትና አስተያየት እየሰጡ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አጠናቃሪ ቡድኑ ዛሬ ማምሻውን እነዚህን የተሰበሰቡ አስተያየቶች በማካተት የመጨረሻውን ሰነድ አጠናቆ እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት ነገ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የተጠናቀረው የመጨረሻ ሰነድ ለአራት ሺህ የጉባኤው ተሳታፊዎች በጋራ የሚቀርብ ሲሆን፣ይህም ሂደቱ ትልቅ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ህዝቡ አንዳንዶች የሚያሰራጩትን የተዛባ መረጃ በመስማት እንዳይወዛገብ እና ለትክክለኛ መረጃዎች የኮሚሽኑን መግለጫዎች ብቻ እንዲከታተል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም