ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል ዜጎች ያለ እንግልት የሚገለገሉበት ነው

አሶሳ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፡- መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል ዜጎች  ያለ እንግልት የሚገለገሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አራተኛው የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ ጀምሯል።


 

ማዕከሉ ስራ በጀመረበት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ  ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ ተገኝተዋል።

‎የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በወቅቱ እንደተናገሩት፣በበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በ8 ተቋማት እና 36 አገልግሎቶች ስራ ጀምሯል።

‎በለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ወደሥራ የገባ አራተኛው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲሆን በቀጣይም አገልግሎቱን በመጨመር የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።‎

በክልሉ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ  በ124 የአገልግሎት ዘርፎች ከ53 ሺ 900 በላይ ዜጎች የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

‎‎የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎቱ ቁልፍ የሆኑ  የክልልና የፌደራል ተቋማትን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

‎የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ በበኩላቸው፤  የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ በሥርዓት ወደ ሚመራ ተቋማዊ ብቃት እየተሸጋገሩ መሆኑን መሶብ የአንድ ማዕከል አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

‎‎የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት በመንግስት   ተቋማት በሚሰጠው አገልግሎት የዜጎች እርካታን ማሳደግ ሲቻል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በክልሉ ቀደም  ‎የቤጉ ፣ የአሶሳ እና የባምባሲ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ይታወሳል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም