ቀጥታ፡

ግብፅ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት ልታከብር ይገባል - የጂኦፖለቲክስ ባለሙያ ኤልያስ ዐቢይ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ ግብፅ የአባይ ወንዝን "ለብቻዬ ልጠቀም" የሚል ጊዜው ያለፈበት እሳቤ በመተው፣ የናይል ወንዝ የ86 በመቶ የውሃ ድርሻ ያላትን ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የመልማት መብት ዕውቅና ልትሰጥ እንደሚገባ የጂኦፖለቲክስ ባለሙያው ኤልያስ ዐቢይ ገለጹ።

የጂኦፖለቲክስ ባለሙያውና ደራሲው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ 135 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የዕለታዊ ሕይወታቸውና ሀገራዊ የልማት ህልውናቸው እነዚህን ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብቶች መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብፅ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም ለማድረግ የምታደርገው ተደጋጋሚ ጥረት መልክአ-ምድራዊ እውነታንና የፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም መርሆዎችን ያላገናዘበ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

ግብፅ ለፍትሐዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም መርሆዎች ተገዢ አለመሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም የሚመነጨው የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት "የእኔ ብቻ ነው" ከሚል ጊዜው ያለፈበትና ዘመኑን የማይመጥን እሳቤ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ፣ በባሮ-አኮቦ እና በተከዜ ተፋሰሶች አማካኝነት ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራትም፤ ግብፅ ግን የቀጣናውን የጂኦፖለቲክስ ውጥረቶችና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎችን መሣሪያ በማድረግ የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎችና የሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ልማት ፕሮጀክቶችን ስታደናቅፍ ቆይታለች።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ይህ ዓይነቱ የማደናቀፍ አካሄድ ከኢትዮጵያ የውሃ መሠረተ ልማት የሚገኘውን ግልጽ አካባቢያዊና ቴክኒካዊ ጥቅሞች ለረጅም ጊዜ ችላ ያለ ነው።

ውሃ በኢትዮጵያ ቀዝቃዛና ጥልቅ ሸለቆዎች ውስጥ በመከማቸቱ በሰሃራ በረሃ በሚገኘው የናስር ሀይቅ ላይ በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የውሃ ትነትና መባከን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

ከአስዋን ግድብ በስተጀርባ የሚገኘው የናስር ሀይቅ በዓለማችን እጅግ ሞቃታማ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ በሆነው በሰሃራ በረሃ ውስጥ ወደ 6,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ቦታ እንደሚሸፍን አመልክተዋል።

በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በዓመት ከ10 እስከ 15 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚባክንና ይህም ሙሉ በሙሉ የባሮ-አኮቦ ወንዝ ወደ ነጭ ዓባይ ከሚወስደው የውሃ መጠን ጋር እኩል መሆኑን ያስረዱት።


 

ከዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የጨመረው የሙቀት መጠን ይህ የውሃ መባከን የበለጠ እንዲባባስ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የውሃ ብክነትና ትነትን ከመቀነስ አንጻር ያላትን ሚና አጉልተው አሳይተዋል።

የሀገሪቱን የወደፊት ስትራቴጂካዊ ጉዞ አስመልክቶ ኤልያስ እንደገለጹት፤ የውስጥ ጥንካሬ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሀገራዊ አንድነት ለውጭ ጫናዎችና ተቃውሞዎች ኢትዮጵያ የምትሰጠው ዋናና ውጤታማ ምላሾች ናቸው።

ሁሉን አቀፍ ልማትን ማፋጠን እና ሀገራዊ ውይይትን ማጎልበት ዘላቂ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

ይህም በበለጸገች ኢትዮጵያ አማካኝነት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስርና ሰላም እንዲሰፍን አስተማማኝ መሠረት ይጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም