በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አራተኛ የሆነው የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አራተኛ የሆነው የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመረቀ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ) ፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አራተኛ የሆነውን የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ መርቀው ከፍተዋል።
አቶ ጌታሁን አብዲሳ ማዕከሉን በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል የዜጎችን እንግልት የሚያስቀር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው።
የበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ አራተኛው ማዕከል መሆኑን ገልጸው ፣ የቤጉ መሶብ፣ የአሶሳ እና የባምባሲ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ቀደም ሲል ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል።
በክልሉ በተዘረጋው ዘመናዊ የአገልግሎት ስርዓት እስካሁን በ124 የአገልግሎት ዘርፎች ከ53 ሺ 900 በላይ ዜጎች የዲጂታል አገልግሎት ያገኙ ሲሆን፣ የእርካታ ደረጃውን 99.2 ከመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በሁሉም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ቁልፍ የክልሉና የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት በአንድ ማዕከል መስጠት መቻሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
አሰራሩ መንግሥት ለዜጎቹ የሚያቀርባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ከብልሹ አሰራር የፀዱ ከማድረጉም ባሻገር በጥራትና በፍጥነት አገልግሎቱን ለመስጠት ማስቻሉን ገልጸው ይህም ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን አመኔታ እንደሚያሳድግም ጠቁመዋል።
ህዝቡ እየታየ ያለውን ሰላም ወደ ዘላቂነት ለማሻገር ከፀጥታ አካላት ጋር ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ጌታሁን አሳስበዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካለች አልቦሮ በበኩላቸው፣ የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በቴክኖሎጂ በሥርዓት ወደሚመራ ተቋማዊ ብቃት ለመሸጋገር መሶብ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገለጸዋል።
የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት በመንግስት ተቋማት በሚሰጠው አገልግሎት የዜጎችን እርካታ ማሳደግ ሲቻል እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሳዬ አበበ፣ የማዕከሉ ሥራ መጀመር በዜጎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳድር ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።
አመራሮቹ በበለስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።