ምክክሩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሀገሪቱ መፃኢ እድል ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሀገሪቱ መፃኢ እድል ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን-ነዋሪዎች
ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሀገሪቱ መፃኢ እድል ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቦንጋና ታርጫ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ለቆዩ አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በጋራ መክሮ ለመፍታት እንደሚያስችል የታመነበት የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
አካታችና አሳታፊነቱ ጎልቶ የታየበት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በታሪክ የታየውን ልዩነት በሰለጠነ መንገድ በመወያየት የሚሰጣቸው የመፍትሔ ሀሳቦች ሀገራዊ መግባባትን እንደሚፈጥሩ በህዝቦች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋና የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ምክክሩ የነበሩ አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር በመፍታት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም፤ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሀገሪቱ መፃኢ እድል ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
የቦንጋ ከተማ ነዋሪው አቶ ታሪኩ ታዬ፤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ታሪካዊና ለረጅም ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሀገራችንን መፃኢ እድል የሚወስን መሆኑን ተናግረዋል።
ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የተወከሉ ኢትዮጵያውያን በጋራ ቁጭ ብለው በጠረጴዛ ዙሪያ መምከራቸው በሀገራቸው ጉዳይ ያገባኛል የሚል እምነት እንዲኖራቸውና የመፍትሔው አካል መሆን የሚያስችላቸው ትልቅ እድል እንደሆነም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ፤ ምክክሩ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ሰላምና አንድነት ፋና ወጊ ሀገር ሆና ሳለች የውስጥ ችግሮቿን በውይይትና በምክክር መፍታት ተስኗት የቆየችበትን ታሪክ በማደስ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገርበት ትልቅ ዕድል ነው።
የምክክር መድረኩ ለዘመናት ሳይፈቱ የቆዩ ውስብስብ ችግሮችን ተወያይቶ ለመፍታትና ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር የሀገርን ሰላምና እድገት እንደሚያጠናክር ተስፋቸውን የገለጹት ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ ደመረ ጌታሁን ናቸው።
ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተወካያቸው አማካይነት የተሳተፉበት መሆኑ ለሀገር ሰላምና ብልፅግና በአንድነት መቆም የሚያስችል ውጤት እንደሚያመጣ እምነታቸው መሆኑን ነው የገለጹት።
በዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ ነዋሪው አቶ አብርሃም አሳሮ በበኩላቸው፤ ምክክሩ እየተካሄደባቸው ባሉት አጀንዳዎች የሚደረሱ ውጤቶች በኢትዮጵያ የነበሩ በርካታ አለመግባባቶች፣ መቃቃሮችና አለመደማመጦችን በዘላቂነት የሚፈቱ እንደሚሆኑ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ እየተካሄደ መሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎችና ሐሳቦች በተወካዮቻቸው በኩል እንዲነሱ ያስቻለ በመሆኑ አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ሀገራዊ መግባባትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ምክክሩ እኔ የሚለውን ነጠላ ትርክት እኛ በሚለው የወል ትርክት በመተካት ሀገራዊ እይታን ያጎላል ያሉት አቶ አብርሃም፤ ይህም ኢትዮጵያውያን ለሀገር ሰላምና ልማት በጋራ መቆም የሚያስችላቸው ወርቃማ እድል መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችንና ችግሮችን ከምንጫቸው በሰለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት በአብሮነትና በአንድነት ወደፊት ለመራመድ ያስችለናል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ዘሪሁን ለማ ናቸው።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክና ችግሮቿን በውስጥ አቅም መፍታት የሚያስችሏት የበርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤት መሆኗን የገለጹት አቶ ዘሪሁን፤ ምክክሩ በዚህ ላይ የተመሰረተና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ተስፋን የያዘ አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።