ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ የታነጹ የነገ ሀገር መሪዎችን የምናዘጋጅባቸው ተቋማት ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ የታነጹ የነገ ሀገር መሪዎችን የምናዘጋጅባቸው ተቋማት ናቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ የታነጹ የነገ ሀገር መሪዎችን የምናዘጋጅባቸው ተቋማት መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በመግለጫቸው እንዳሉት በትምህርት ሚኒስቴር የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ላላቸው ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የተቋቋሙ ተቋማት ናቸው።
ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት በወሊሶ፣ በቡኢ፣ በቦንጋ፣ ጋምቤላና ጅግጅጋ አጠቃላይ በ5 የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በእያንዳንዱ እስከ 250 ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱ አስታውሰዋል።
በዘንድሮው ዓመት 4 ተጨማሪ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመገንባት በባህርዳር፣ አርባ ምንጭ፣ አሶሳና ድሬዳዋ አጠቃላይ በ9 አዳሪ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ቅበላ ይከናወናል ብለዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተወዳድረው ያለፉ ተማሪዎች በመቀበል የተሻለ ትምህርት የሚያገኙበት እድል መሆኑን ጠቁመዋል።
ማንኛውም ብቃትንና ጥንካሬን በሚለካው የመግቢያ ፈተና በማረጋገጥ እኩል የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ እንደሚደረግም ጨምረው ገልፀዋል።
በመሆኑም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በልዩ ትኩረት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ የታነጹ የነገ ሀገር መሪዎችን የምናዘጋጅበት ተቋም ነው ብለዋል።
በቀጣይም አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
የመግቢያ መስፈርቶቹ የ8ኛ ክፍል ውጤት ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
በዚህም የተማሪዎች ወላጆችና ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊው የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ፖርታል አማካኝነት እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርበዋል።