የምክክር ጉባኤው የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን የሚገነባ ድልድይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን የሚገነባ ድልድይ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ፣ ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን የሚገነባ ድልድይ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በምክክሩ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ምክክር በማካሄድ ወደ የጋራ መግባባት እየደረሱ ይገኛሉ።
ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የምክክር ጉባኤው በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የመግባባት ባህልን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት እየጣለ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ፣ ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን የሚገነባ ድልድይ መሆኑን ገልጸዋል።
ተመካካሪ አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር)፣ የምክክር ጉባኤው የተለያየ ሀሳብ ያላቸው የአንድ ሀገር ሕዝቦች በአንድ መድረክ ተሰባስበው የሚመካከሩበት ነው ብለዋል።
በምክክር ጉባኤውም የአንድ ሀገር ሕዝቦች የተለያዩ ሀሳቦችና አመለካከቶች ቢኖሯቸውም፣ በጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የጋራ መፍትሔ ማፍለቅ እንደሚቻል መሠረት የጣለ ስልጡንና ታሪካዊ ሀገራዊ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ልምምዱ እየጎለበተ ሲመጣም ለሀገር የሚበጁ ምክረ ሀሳቦችን በማፍለቅ፣ የጋራ መግባባት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ ድልድይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ተመካካሪዎችም አንዱ የአንዱን ሀሳብ በመገንዘብና በመደማመጥ፣ የሕዝብን የጋራ አሸናፊነት የሚያረጋግጡ ምክረ ሀሳቦችን ለማፍለቅ የሚያስችል ውጤታማ ምክክር እያካሄዱ መሆኑን አንስተዋል።
ለቀጣዩ ትውልድም የምክክርና የመግባባት ባህልን ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየተጣለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተመካካሪ ፋጡማ ይማም በበኩላቸው፣ የምክክር ጉባኤው በ10፣ በ50፣ በ250 እና በ500 የምክክር ቡድን አደረጃጀቶች በመከፋፈል አካታችና አሳታፊ ምክክር እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው የቡድን አደረጃጀትና የምክክር ሂደት ተመካካሪዎች በነፃነት ሀሳባቸውን እንዲያነሱ፣ በጋራ እንዲመክሩና የጋራ መግባባትን የሚያጎለብቱ መፍትሔ እንዲያፈልቁ ዕድል እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱ አሳታፊና አካታችነትም የጉባኤውን ሙሉነት እንደሚያሳይ አንስተዋል።
የምክክር ጉባኤው የእርስ በርስ መደማመጥና አንዱ የአንዱን ሀሳብ የሚገነዘብበትን ዕድል የፈጠረ ወሳኝ መድረክ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አቶ አብዲ ከድር ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የመማከርና የመደማመጥ ዕድል በበቂ ሁኔታ አለመፈጠሩ ሀገር ውድ ዋጋ እንድትከፍል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤም በመደማመጥና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ዕድል እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።