ከሰመራ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተናል-ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
ከሰመራ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተናል-ተገልጋዮች
ሰመራ፣ ነሀሴ 13/2018 (ኢዜአ)፡-የሰመራ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋቱ ጊዜና ገንዘባቸውን ለመቆጠብ መቻላቸውን ተገልጋዮች ገለጹ።
ማዕከሉ ጉዳይ ለማስፈጸም የተለያዮ ቢሮዎች ለመሄድ ይገደዱ የነበረበትን አሰራር ማስቀረቱን የተናገሩት ተገልጋዮቹ፣ በአሁኑ ወቅት በአንድ ቦታ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የማዕከሉ ተገልጋዮች መካከል አቶ ኢብራሂም አሚን የንግድ ፈቃድ ለማደስና ግብራቸውን ለመክፈል ወደማዕከሉ እንደመጡ ገልጸዋል።
በማዕከሉም ሁሉንም አገልግሎት ፈጣን በሆነ መንገድ እንዳገኙ ገልጸው ይህም ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ጉዳይ ለማስፈጸም ወደተለያዩ ቢሮዎች ሲሄዱ ይደርስባቸው የነበረን ወጪና እንግልት አስቀርቷል ብለዋል።
ቀደም ሲል ጉዳይ ለመፈጸም በርካታ ቀናት ሲወስድባቸው እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ጉዳያቸውን እንደጨረሱ ተናግረዋል።
በማዕከሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋቱ በርካታ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ማግኘት እንደቻሉና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ዓሊ ኢብራሂም ናቸው።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩትን ብልሹ አስራሮችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱን ጠቁመው፣ በማዕከሉ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የንግድ ፍቃድ ለማውጣት የሚያስችል የመለያ ቁጥር ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ማውጣት እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ መርዲያ ኑርሁሴን እና ፋጡማ ሀቢብ ናቸው።
በዚህን ያህል ፍጥነት አገልግሎቱን እናገኛለን ብለው ያስቡ እንዳልነበር ገልጸው፣ በማዕከሉ ፈጣን አገልግሎት ከጥሩ መስተንግዶ ጋር በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የሰመራ ከተማ ሞሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ከሊል ዓሊ በበኩላቸው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልል ደረጃ መሰጠት መጀመሩን ገልጸዋል።
ይህም በተለያየ ቦታ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ባንድ ቦታ በዲጂታል አሰራር ታግዞ ለመስጠት አስችሏል ብለዋል።
ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉ በተጨማሪ የተገልጋይን ጊዜና ገንዘብ ከብክነት እየታደገ መሆኑንም ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ዘመኑን የዋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልል ደረጃ መሰጠት የጀመረውን አገልግሎት በሰመራ ሎጊያ፣ በአዋሸ ሰባት እና በአይሳኢታ ከተሞች ለማስፋፋት የማዕከላት ግንባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አብአላ፣ ዱብቲ፣ ሚሌ፣ ጭፍራ እና ወረር አዳብቶሌ ከተሞች የቦታ መረጣና ልየታ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ግንባታቸውን በመከናወን ላይ ያሉት ማዕከላት በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓምት ድረስ አገልግሎት ለማስጀመር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሰመራ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአምስት ተቋማት ዘጠኝ አገልግሎቶች ስራውን መጀመሩን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት የሚሰጡ አገልግሎቶች ወደ 41 ከፍ ማለታቸውንና በቀጣይም ወደ 80 ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል።
በማዕከሉ አገልግሎት ከሚሰጡት ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፣ ገቢዎች ቢሮ፣ ፍትህ ቢሮ እንዱሁም ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) እንደሚገኙበት ገልጸው፣ እስካሁንም በማዕከሉ 20 ሺሀ 463 ተጠቃሚዎች አገልግሎት አግኝተዋል ብለዋል።