ቀጥታ፡

ከውጭ የሚገባውን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተመዘገበ ነው

ጂንካ፤ ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ ከውጭ የሚገባውን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጥጥ ምርት በስፋትና በጥራት ለማምረት የግል ባለሀብቱን ያሳተፈ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን በጥጥ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የስራ እንቅስቃሴን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ጎብኝተዋል።

የቢሮ ኃላፊው በወቅቱ እንዳሉት፤ ከውጭ የሚገባውን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የተጀመረው ጥረት አበረታች ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

በክልሉ ጥጥን ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን ለማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለም ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ የጥጥ ምርትን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ረገድ የናሳ እርሻ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ልማታዊ ባለሀብቶችን በማበረታታት የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት መሪ ተዋናይ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት የማያቋርጥ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ በበኩላቸው፤ የደቡብ ኦሞ ዞን ለጥጥ እርሻ ልማት ተስማሚ የሆነ ስነ-ምህዳር ያለው በመሆኑ የግል ኢንቨስትመንቶች በጥጥ እርሻ ልማት ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በጥጥ ልማት በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ ኢንቨስተሮች የናሳ ብራይሌ እርሻ ልማት ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ከሚፈጥረው የስራ ዕድል ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዞኑ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የመምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል።

የናሳ ብራይሌ እርሻ ልማት በደቡብ ኦሞ ዞን በባና ፀማይ ወረዳ የወይጦ ወንዝን በመጥለፍ ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ጥጥ እያመረተ እንደሚገኝ የተናገሩት የእርሻ ልማቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አረጋዊ ገብረስላሴ ናቸው።

ድርጅቱ በዋናነት የሀገሪቱን የጥጥ ምርት ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለመተካት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የእርሻ ልማቱ ለሀገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ከማቅረብ ባለፈ፣ በአካባቢው ባስገነባው የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለ300 ቋሚ እና 3 ሺህ ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም