በምክክር ጉባኤው ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ነገ የሚያሻግሩ ምክረ ሃሳቦችን በነፃነት በማንጸባረቅ እየተመካከርን ነው - ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር ጉባኤው ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ነገ የሚያሻግሩ ምክረ ሃሳቦችን በነፃነት በማንጸባረቅ እየተመካከርን ነው - ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ነገ የሚያሻግሩ ምክረ ሀሳቦችን በነፃነት በማንጸባረቅ እየተመካከሩ መሆናቸውን ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ ምክክር እያካሄደ ነው።
በምክክር ጉባኤውም ያለአንዳች ጣልቃ ገብነት ሀሳባቸውን በነጻነት በማንጸባረቅ ለኢትዮጵያ የሚበጁ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሰብሳቢና የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ፈይሰል አብዱላዚዝ እንዳሉት፤ ምክክር ሁነኛ የመግባቢያ መንገድ ነው።
በስምንቱ ዐበይት የምክክር አጀንዳዎች ላይ ለሀገራዊ መግባባት የሚበጁ ምክረ ሀሳቦችን በሙሉ ነፃነት በማንጸባረቅ እየተመካከሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የጉባኤው ተመካካሪዎችም አንዱ የአንዱን ሀሳብ እንዲገነዘብ በማስቻል ኢትዮጵያን ለዘመናት የፈተኗትን የአለመግባባት ችግሮች በጋራ አሸናፊነት ለመቋጨት ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
መድረኩም ለትውልድ የሚተርፍ የሰለጠነ የምክክር ባህልን ለመገንባት መሠረት የሚጥል ተመራጭ አካሄድ መሆኑን አንስተዋል።
ከሕዳሴ ፓርቲ የምክክር ጉባኤው ተመካካሪ እንዳልካቸው አረጋ በበኩላቸው፤ በአካታችና አሳታፊ የምክክር ጉባኤው ላይ ሀሳባቸውን በነፃነት በማንጸባረቅ ለሀገር የሚበጁ ሀሳቦችን እያዋጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤውም የኢትዮጵያን የዘመናት ችግሮች በመሻገር ሀገራዊ መግባባት የሰፈነባትን ሀገር መገንባት የሚያስችል ትምህርት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክሩ አጀንዳዎች ላይ ያለአንዳች ጣልቃ ገብነት ሀሳብን በነፃነት በማዋጣት ሰላማዊትና የጋራ መግባባት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት እየመከርን ነው ብለዋል።
ጉባኤው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጽ የሚሰማበትን ዕድል በመፍጠር ለሀገር ከፍታ የሚበጁ ምክረ ሀሳቦች እየተንጸባረቁበት ነው ያሉት ደግሞ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተመካካሪ ሰለሞን ታፈሰ ናቸው።
በምክክሩም ለዘመናት የተከማቹ ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ መግባባት እልባት በመስጠት ሰላምና ዕድገቷን የምታፋጥን ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል የአንድነት ድልድይ መሆኑን ገልጸዋል።
የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዋና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና ተመካካሪ መምህር ሰለሞን ሀኒባል በበኩላቸው፤ ጉባኤው ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን ፈታኝ ጊዜያት መሻገር የሚያስችል መሠረት ይጥላል ብለዋል።
በተመካካሪዎች መካከልም ነፃ፣ አካታችና አሳታፊ የሀሳብ ፍጭት እየተንጸባረቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር ጉባኤው ዐበይት አጀንዳዎችም የሀገርን የጋራ አሸናፊነት የሚያበስር የጋራ መግባባት ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።