የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ ሕወሃትን ከጫንቃው በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን አለበት - ሌተናል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ ሕወሃትን ከጫንቃው በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን አለበት - ሌተናል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ ሕወሃትን ከጫንቃው በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን እንዳለበት የቀድሞው ወታደራዊ አመራር ሌተናል ጀኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል ተናገሩ፡፡
የቀድሞው ሕወሃት መስራች አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ትናንት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሕገ -ወጡ ሕወሃት አመራሮች ጊዜው ሳይረፍድ እጃቸውን ለፌደራል መንግስት መስጠት እንዳለባቸው መናገራቸው ይታወሳል።
የሕገ-ወጡ ሕወሃት አመራሮች ለታሪካዊ ጠላቶች በመላላክ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ እየፈጸሙ መሆኑንም አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ማንሳታቸው ይታወቃል።
ከጥፋት ቡድኑ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞው ወታደራዊ አመራር ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ 'ጽምዶ'' በሚል ስያሜ የተሰባሰቡ ኃይሎች በሥልጣን ጥማት የሰከሩና እርስ በእርሳቸው የማይተማመኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጥምረቱም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ጉዞ የማዳከም ዓላማ በማንገብ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች የወጠኑት መሆኑን ተናግረዋል።
የሻዕቢያ ኃይል ከጥፋት ውጪ የልማትና ዕድገት ትብብር አይታየውም ያሉት ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ፤ ኤርትራንም የልማት ሽታ የማይውቃት የስደት፣ ሞትና እንግልት ምድር አድርጓት መቀጠሉን አንስተዋል።
የሕገ-ወጡ ሕወሓትን፣ የኦሮሚያና አማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎችን ''ጽምዶ'' በሚል ስያሜ ያለ አንዳች ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለጥፋት ዓላማው ማስፈጸሚያነት በማጣመር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የ''ጽምዶ'' ጥምረትም ተስፋ መቁረጥ የወለደው ያለአቻ ጋብቻ የጥፋት እንቅስቃሴ መሆኑን አብራርተዋል።
የ''ጽምዶ'' ጥምረትም በሻዕቢያ የበላይ ጠባቂ ኢሳያስ አፈወርቂ ቀጭን ትዕዛዝ የሚመራና በራሱ የመወሰን አቅም የሌለው፣ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ታሪካዊ ጠላቶች ዓላማ አስፈጻሚ ነው ብለዋል።
የጥፋት ጥምረቱ በታሪካዊ ጠላቶች በሚሰፈርለት ቀለብ ልክ የሚያሰራጨው ስሁት ፕሮፓጋንዳም ሕዝብን በማወናበድ ላይ የተመሠረተ መሠረተ ቢስ ስብስብ መሆኑን በተግባር እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በጥፋት ጥምረቱ የ''ጽምዶ'' ስብስብ የፈጠረው ያልተቀደሰ ጋብቻም ከጥፋት አጋሩ ሻቢያ የቀሰመው የአጥፍቶ ጠፊነት ባህሪ መሆኑን አንስተዋል።
የትግራይ ሕዝብ ጠላት በክልሉ በቅሎ ከጎለመሰው ሕገ-ወጡ የሕወሓት ስብስብ በተጨማሪ ሻዕቢያ አንደኛው መሆኑም አስገንዝበዋል።
የትግራይ ህዝብ ሕገ ወጡ ሕወሃትን ከጫንቃው ላይ በማውረድ ሰላምና ልማትን ማፋጠን እንደሚኖርበት አስረድተዋል።
በትጥቅ ትግል ታግዞ የሚካሄድ ኋላቀር የጠብመንጃ እንቅስቃሴ ሀገርና ሕዝብን ከማጎሳቆል የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው አስረድተዋል።