ቀጥታ፡

ሕወሓትን እንደ አሞሌ ጨው ቀምሰን አይተነዋል፤ ከግጭት ውጭ አንድም የሚጠቅም ሀሳብ የለውም – የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጁነዲን ሳዶ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ) ፦ ሕወሃትን እንደ አሞሌ ጨው ቀምሰን አይተነዋል፤ ከግጭት ውጭ አንድም የሚጠቅም ሀሳብ የለውም ሲሉ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጁነዲን ሳዶ ገለጹ።

አቶ ጁነዲን ሳዶ፤ ሕገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ሀገር በሚያስተዳድርበት ዘመንም አንዱን ሕዝብ ከሌላው ጋር በማቃረን ለሕዝቦች መቃቃር ምክንያት ሲሆን መቆየቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

አሁን ላይም በታሪካዊ ጠላቶች በመታዘል የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ሰቆቃና መከራ ዳርጎታል ነው ያሉት።

ሕወሓትን እንደ አሞሌ ጨው ቀምሰን አይተነዋል፤ አብረንም ሰርተናል፤ ከግጭትና ጥፋት ውጪ ለሀገር የሚጠቅም አንድም ሀሳብ የለውም ብለዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የዘመናትን የግጭት አዙሪት ከማስቀጠል ውጭ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አንድም አዎንታዊ ሀሳብ የሌለውና ሀገርን ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፈ አጥፊ ስብስብ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ህገ-ወጡ ቡድኑ "እኔ ካልገዛሁ" የሚለውን ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ተሸክሞ ታጣቂ በማደራጀት ሀገር ለማመስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የትም የማያደርሰው ከንቱ ልፋት መሆኑንም አስረድተዋል።

በየትኛውም ሀገር አንድ ሕጋዊ ሠራዊት ብቻ የሚኖር መሆኑ እየታወቀ ቡድኑ እየተከተለው ያለው የትዕቢትና የአጥፊነት መንገድ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚያጋጨው መሆኑንም ገልጸዋል።

ህገ-ወጥ ቡድኑ ያለው አማራጭ ከጥፋት ጎዳናው ተመልሶ ወደ ሰላም መስመር መምጣት ብቻ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም