የቤቶች ልማት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ አካታች አካሄድ ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቤቶች ልማት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ አካታች አካሄድ ተግባራዊ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የቤት ልማት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ አካታች አካሄድ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የሚችሉበት አዋጅ ቁጥር 1388/2017 ቀደም ሲል መጽደቁ ይታወሳል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በአዋጁ መሠረት የተዘጋጀውን መመሪያ የማስተዋወቂያ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር የማስተዋወቅ ውይይት አካሂዷል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤቶችን አቅርቦት ለማስፋት ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ የቤት አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋት እየተሠራ ነው።
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችለው መመሪያ የቤት ልማት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና በሁሉም አካባቢዎች ተመጣጣኝ ዕድገትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ሀገራት ተጨማሪ የካፒታል ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የውጭ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግን እንደ አንድ መንገድ እንደሚጠቀሙ ጠቁመው፣ በኢትዮጵያም ኢኮኖሚውን ክፍት በማድረግ የውጭ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አዋጅ መውጣቱን አንስተዋል።
የቤት ልማት አቅርቦትን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማስፋት፣ የሥራ ዕድልን ማስፋትና የክልል ከተሞች ተመጣጣኝ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ከአዋጁ ጠቀሜታዎች መካከል እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
አዋጁን ለመተግበር የተዘጋጀውን መመሪያ መሠረት በማድረግ ሁሉም ተቋማት ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግና ወደ ተቀናጀ እንቅስቃሴ መግባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጸጋዬ ሞሼ ባቀረቡት ማብራሪያ መመሪያው ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ የውጭ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ሥርዓት ለመዘርጋትና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባና ሸገር ከተሞች የውጭ ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ዝቅተኛው የግዥ ዋጋ 150 ሺህ ዶላር ሲሆን፣ በሌሎች ክልሎች ከተሞች ደግሞ ከ100 ሺህ እስከ 120 ሺህ ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ከወንጀል ነፃ ማረጋገጫ፤ የሰላምና ደኅንነት ማረጋገጫ ሰነዶች፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተሰጠ ሕጋዊ የኢንቨስትመንት ፈቃድና የጽሑፍ ማረጋገጫ፣ ፓስፖርትና ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
በመመሪያው አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት፣ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታትና ሕገ-ወጥ አሠራርን ለመከላከል የፋይናንስ ደኅንነትና ቁጥጥርን ለማጠናከር እንደሚሠራና የመመሪያ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ጠንካራ ተጠያቂነት እንደሚኖር ተነስቷል።