ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሕጻናትን የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት እጥረት በመቀነስ ውጤታማ ሥራ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሕጻናትን የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት እጥረት በመቀነስ ውጤታማ ሥራ እየሰራች መሆኗን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ በ11 የአፍሪካ ሀገራት የሕፃናት የምግብ እጥረትን ለመከላከል የተደረገውን የሦስት ዓመት ፕሮግራም ግምገማና የልምድ ልውውጥ እያካሄደ ነው።

የሦስት ዓመት ፕሮግራም ግምገማና የልምድ ልውውጥ መድረክም ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር መብራቱ ማሴቦ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ሀገራት የሕፃናትን የምግብ ደኅንነት የሚያረጋግጥ ትብብር በመገንባት በትኩረት መሥራት አለባቸው።

የአህጉሪቷን የሕፃናት የምግብ እጥረት ለማስተካከል የተደረገው የሦስት ዓመት ፕሮግራም የአፍሪካ ሀገራትን ጥረት በመደገፍ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህ በኩል በኢትዮጵያ የሕፃናትን አጣዳፊ የምግብ እጥረትን (መቀጨጭን) ለመቀነስ ውጤታማ ስራ ከሚሰራባቸው የአህጉሪቷ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

በቀጣይም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን የበለጠ በማሳደግ የሕፃናትን ሁለንተናዊ የምግብ ደኅንነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የሚሲዮን ኃላፊ፣ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ በበኩላቸው፤ የልጆች አመጋገብ የትውልድ ግንባታን የሚወስን ወሳኝ ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕፃናትን የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥም ሀገራት የውስጥና የልማት አጋሮችን አቅም በመጠቀም ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

መድረኩም የሕፃናትን የዕድገት ሁኔታ የሚወስን የጋራ መግባባት፣ ልምድና ተሞክሮን በመቀመር ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም