ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ጥራት ላለው የትምህርት ተደራሽነት በጥናት የተደገፈ የቁጥጥርና የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

ድሬደዋ፣ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር ጥራት ላለው የትምህርት ተደራሽነት በጥናት የተደገፈ የቁጥጥርና የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

የትምህርት ቢሮ በግል ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ባዘጋጀው የጥናት ሰነድ ላይ ከግል ትምህርት ቤቶች ባለቤቶችና አመራሮች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በድሬዳዋ አስተዳደር ጥራት ላለው የትምህርት ተደራሽነት በጥናት የተደገፈ የቁጥጥርና የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። 

በዚህም በአስተዳደሩ በሚገኙ የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወጥ የሆነ አሰራርና አደረጃጀት በጥናት ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በክፍል ዝውውር፣ በምዘና፣ በማለፊያ ነጥብ አሰጣጥና በተማሪዎች ሽግግር ላይ ጥራትን መሠረት ያደረገ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

ቢሮው በመጪው የትምህርት ዘመንም በጥናት የተደገፈ አሰራርን በሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች በመተግበር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች በቅድመ መደበኛና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ወጥና ዘላቂ አሰራርና አደረጃጀትን ለማስፈን የሚያስችል ጥናት መዘጋጀቱንም ኃላፊው አብራርተዋል። 

ዛሬ በተካሄደው ውይይት የቀረበውን የጥናት ሰነድ ባለሃብቶችና የትምህርት ቤቶቹ አመራሮች በአግባቡ ለመተግበር የጋራ መግባባት መፍጠራቸው በቀጣዩ ዓመት ውጤታማ ሥራ ለመስራት መደላድልን ይፈጥራል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች መካከል አቶ ኤልያስ መለስ እንዳሉት፤ የተዘጋጀው ጥናት የትምህርት ፖሊሲውን በወጥነት በመተግበር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያስችላል። 

ይህም የትምህርት አሰጣጥ ክትትልና ቁጥጥርን በማሻሻል የላቀ ውጤት ለማምጣት አጋዥ ነው ብለዋል።

አቶ ኢድሪስ አደም የተባሉ የትምህርት ቤት ባለቤት በበኩላቸው፤ በጥናት የተለዩት ክፍተቶች በመምህራን፣ በተማሪዎችና በወላጆች ቅንጅት ለመፍታት አቅጣጫን የሚያመላክቱ መሆናቸውን አውስተዋል። 

ችግሩን  በመጻሕፍት ሥርጭትና በመምህራን ልማት ላይ በመስራት ለመፍታትና ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም