ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የጨረር ቴክኖሎጂን ከህክምናው በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ እየተጠቀመች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የጨረር ቴክኖሎጂን ከህክምናው በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ እየተጠቀመች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ጌታቸው (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን በህክምናው ዘርፍ ለምርመራ ዓላማ ጥቅም ላይ እየዋለ በሚገኘው የጨረር ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ወርክሾፕ አካሂዷል።


 

በወርክሾፑ ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰሎሞን ጌታቸው እንዳሉት ባለስልጣኑ ቁጥጥር ከሚያደርግባቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል የጨረር ቴክኖሎጂ አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የጨረር ቴክኖሎጂን በህክምናው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ እየተጠቀመች እንደምትገኝም ተናግረዋል።

ዶክተር ሰሎሞን ጌታቸው በጥናታቸው እንዳመላከቱት የጨረር ቴክኖሎጂ ለህክምና ምርመራ ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት የጨረር መጠን አጠቃቀም ከቦታ ቦታ እና ከባለሙያ ባለሙያ መለያየት መስተዋሉን ጠቁመዋል።

ይህም በጨረራ ቴክኖሎጂ እና በሌሎች የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የህክምና ተገልጋዮች ላይ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል።

በህክምና ዘርፉ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ትክክለኛውን መጠን ግምት ውስጥ ያስገባ የጨረራ ቴክኖሎጂን ለምርመራም ሆነ ለህክምና አገልግሎትን መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የጨረር ቴክኖሎጂ ለህክምና ምርመራ ሲውል የታካሚውን ወቅታዊ የጤና እና የአካል ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በጥናቱ በአማካሪነት የተሳተፉት ፕሮፌሰር ሰይፈ ተፈሪ ናቸው።


 

ጥናቱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እና በህክምናው ዘርፍ መሳተፍ የሚገባቸውን ባለሙያዎች ማሳተፉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የህክምና ተቋማት የጨረር ቴክኖሎጂን ለህክምና ምርመራ እየተጠቀምን ብንሆንም ወጥ በሆነ መንገድ እየተተገበረ ባለመሆኑ ጥናቱ ይህን ችግር በመፍታት በኩል የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ሌላኛው በጥናቱ በአማካሪነት የተሳተፉት ፕሮፌሰር ዳንኤል ዘውድነህ በበኩላቸው፤ ጥናቱ በተለያዩ ጊዜያት ሆስፒታሎች በተናጠል ሲያከናውኑት ከነበረው ጥናት በይዘቱም ሆነ በስፋቱ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።


 

የጨረር ቴክኖሎጂን ለህክምና ምርመራ ስንጠቀም ለታካሚውም ሆነ ለዘርፉ ባለሙያ ደህንነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መሆን እንዳለበትም ጥናቱ ምክረ ሀሳብ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም