ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታች በመሆኑ የዜጎችን አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ውጤት እንደሚኖረው ተስፋ እናደርጋለን - የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች

ደብረ ብርሃን፤ ነሐሴ 12 / 2018 (ኢዜአ) ፡- የምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታች በመሆኑ የዜጎችን አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ውጤት እንደሚኖረው ተስፋ ማድረጋቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ ታሪክ በሕዝቦች መካከል የታየውን ልዩነት በሰለጠነ ውይይት ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ አዲስ ምዕራፍ ነው። 

ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽነትና በነጻነት በመወያየት የሚሰጡት የመፍትሔ ሐሳብ፣ ለቆዩ አለመግባባቶች መፍትሄን በመስጠት ለጋራ ዕድገትና አብሮነት ጠንካራ መሠረትን የሚጥል ነው። 

ይህም የምክክር ሂደት አዎንታዊ ውጤት እንደሚያመጣና ለሀገሪቱ የተሻለ ነገን እውን እንደሚያደርግ በሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ እምነትና ተስፋን አጭሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደብረ ብርሃን ነዋሪዎችም የምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታች በመሆኑ የዜጎችን አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ውጤት እንደሚኖረው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፀጋው ገብረመድህን እንደገለጹት፤ የበለጸጉ ሀገራት የእድገት ምስጢር ችግሮቻቸውን በምክክር መፍታት መቻላቸው ነው። 

ችግሮችን በውይይትና በምክክር መፍታት ሀገርን ከነሙሉ ክብሯ ለትውልድ የማስረከብ ኃላፊነትን መወጣት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ምክክሩ ሀገራዊ እሴቶችን በማጉላት በሕዝቦች መካከል አንድነትን፣ ሰላምንና ፍቅርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት እንደሚያስችል ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በላይ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የምክክር ጉባኤው አሳታፊና አካታች በመሆኑ የዜጎችን አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ውጤት እንደሚኖረው እምነቴ ነው ብለዋል። 

ወጣቶችም ከሐሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅና ከጉባኤው የሚወጡ ምክረ ሐሳቦችን በመቀበል ለሀገር እድገት መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የምክክር ጉባኤው ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሂደቱን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የተናገሩት ወይዘሮ ጽጌ አሻግሬ፤ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ለሀገሪቱ አዲስ የሰላምና ብልፅግና ምዕራፍን ይከፍታል የሚል እምነት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ከምክክር ጉባኤውም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር እና ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ጸንተው እንዲቆሙ የሚያደርጉ ሐሳቦች እንደሚወጡ ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም