ቱባ ባህላዊ እሴቶችን በማልማት የባህር ዳር ከተማን የቱሪዝም መስህብነት እናጠናክራለን-ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው - ኢዜአ አማርኛ
ቱባ ባህላዊ እሴቶችን በማልማት የባህር ዳር ከተማን የቱሪዝም መስህብነት እናጠናክራለን-ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 12/2018(ኢዜአ)፡-የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቱባ ባህላዊ እሴቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነት ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መስጠቱን የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ቡሄ እና እንግጫ ነቀላ በዓላት በባህር ዳር ከተማ ደረጃ ዛሬ በድምቀት ተከብረዋል።
የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ባህር ዳር የክልሉ መንግስት መቀመጫ በመሆኗ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ቱባ ባህላዊ እሴቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መስህብነቷን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው፣ አስተዳደሩ በክልሉ ያሉና የህዝብ መገለጫ የሆኑ ቱባ ባህላዊ እሴቶችን ከመጤ ባህሎች ተጠብቀው ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።
በባህር ዳር ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ፤የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ እና ቡሄ ያሉ የህዝብ ባህሎችን በአደባባይ ለማክበር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል።
የከተማዋን ውበትና ገጽታ የሚያጎሉ የልማት ሥራዎችም ለከተማዋ የቱሪዝም ልማት ማደግ መሰረት መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም ልማቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ ባህር ዳር የክልሉን ቱባ ባህሎች ከዘመናዊነት ጋር አጣጥማ ማደግ አለባት።
የባህር ዳር ከተማ ባህልንና ዘመናዊነት ያጣጣመ እድገት በመስመዝገብ "ከተሞች እያደጉ ሲመጡ ባህላቸውን ይዘነጋሉ" የሚለውን እሳቤ መስበር ችላለች ብለዋል።
እውነተኛ ስልጣኔ ያሉንን ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ በመያዝና በማሳደግ ከዘመኑ ጋር አብሮ መራመድ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከናወኑ ተግባራት ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የባህር ዳር ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው በበኩላቸው እንደገለጹት መምሪያው በተለያዩ ምክንያቶች እየተረሱ የመጡ ባህሎች እና ማህበራዊ እሴቶችን ለማልማት በትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህም በሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ደቡብ ጎንደር፣ መስራቅ ጎጃምና ሌሎች ዞኖች የሚከበሩ የክረምት ባህላዊ በዓላት በከተማዋ እንዲከበሩ በማድረግ የማስፋፋት ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ የከተማ አስተዳደሩና የክልሉ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።