ቀጥታ፡

የአዳማ ከተማን የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከልነት ለማሳደግ የግሉ ሴክተር ተሳትፎ እንዲጎለብት ተጠየቀ

አዳማ፤ ነሐሴ 12/2018(ኢዜአ )፡-የአዳማ ከተማን የቱሪዝም የኮንፈረንስ ማዕከልነት ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት የከተማ አስተዳደሩ ቱሪዝም ኮሚሽን ጠየቀ።

በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ድርጅቶች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኩሉ በወቅቱ እንዳሉት፤ የከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግል ዘርፉ ሚና ከፍተኛ ነው። 

ይህን ለማሳካትም የከተማ አስተዳደሩ ለቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።

የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጥራትን ለማሻሻል የተደረገው ቅንጅታዊ ተግባር የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም እያገዘ መምጣቱንም ኃላፊዋ ገልጸዋል። 

በበጀት ዓመቱ ከ27 ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ዜጎች ከተማዋን በመጎብኘታቸው ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በቱሪዝምና ሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት ለሚሹ 119 ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የአዳማ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አጀማ በበኩላቸው፤ የከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማትና የኮሪደር ልማት የቱሪስት ፍሰትና ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ማስቻሉን ገልጸዋል። 

ለዚህም የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል ማድረግና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ማስፋፋት አዎንታዊ ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል። 

በተለይም የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ተደራሽነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የአገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሮቢ ሆቴል ባለቤት አቶ ደምሴ በየቻ እንደገለጹት፤ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ለማስኬድ በጥራትና በተወዳዳሪነት ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። 

ከከተማዋ እድገትና ገጽታ ጋር አብረው የሚሄዱ የቱሪስት አገልግሎቶችን ለማቅረብም አስተዳደሩ የመብራትና የውሃ አገልግሎት ክፍተቶችን እንዲቀርፍላቸው ጠይቀዋል።

የናፍሌት ሆቴል ተወካይ አቶ ደምሱ ይርባ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የቱሪስት ቆይታን ለማራዘም የሚያስችል ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ለዚህም በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ ሆቴሎች ለጎብኚዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል። 

ይህም ተቋማቱ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ተመራጭ እንዲሆኑና አገልግሎቶቻቸውን እንዲያዘምኑ ማገዙን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም