ቀጥታ፡

እንግልትን ያስቀረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

መንግሥት ለዜጎቹ የሚያቀርባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጥራት፣ ፍጥነትና ፍትሐዊነትም የሀገርን ፖለቲካዊ መረጋጋትና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚበይኑ መጋቢዎች ናቸው።

የመደመር መንግሥት ዕሳቤ፤ በተቋማት ግንባታና አገልግሎት ጥራት በመደመር ፍልስፍና ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ግንባታ የሀገር ግንባታ የጀርባ አጥንት ተደርገው ይወሰዳሉ።

በመደመር መንግሥት መፅሐፍ ገፅ-130 እንደሰፈረው፤ ''በየተቋማት ያሉ የመንግስት ሠራተኞች ሕዝቡን ከቢሮክራሲው በላይ የሚመለከቱ እንዲሆኑ ይጠበቃል። አገልጋይነትን የተላበሱ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ይህንን ዕሳቤ በተግባር የሚተረጉም ነው።ግለሰባዊ ንክኪን በመቀነስና አሰራርን በቴክኖሎጂ በመተካት ተቋማት ከግለሰቦች መልካም ፈቃድ ይልቅ በሥርዓት ወደሚመራ ተቋማዊ ብቃት መሸጋገርን ያሳያል።

የአገልግሎት ጥራት መሻሻልም ዜጎች በሀገራቸው ተቋማት ክብራቸውና መብታቸው ተጠብቆ ያለ እንግልት የሚገለገሉበትን ምኅዳር ይፈጥራል።

በተቋማት አገልግሎት የዜጋ እርካታ (Citizen Satisfaction) ዋነኛ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ተደርጎ ይወሰዳል።


 

በሐረሪ ክልልም ዘጠኝ ቁልፍ የክልሉና የፌደራል የመንግሥት ተቋማት በአንድ ጣሪያ ስር መሰባሰባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋግሮታል።

እነዚህ ተቋማት ፦የገቢዎች ፣ የንግድ ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ መሬት ልማት ፣ ኢንተርፕራይዝ ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ፣ኢትዮ ፖስታ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአጠቃላይ 96 አገልግሎቶች ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።ይህም የዜጎች እንግልት በማስቀረት ታላቅ እፎይታን ፈጥሯል።

በማዕከሉ ዜጎች ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን በመቆጠብ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችላል።


 

ይህ ታላቅ ተግባርም ኢትዮጵያ በመደመር ዕሳቤ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥንና ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ ያላቸውን አመኔታ በጽኑ መሠረት ላይ የሚገነባ መሠረት ነው።

ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ዜጎች ምቹ አገልግሎት እየቀረበበት የሚገኘው የሐረሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በውጤታማነቱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ተገልጋዮች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም