ምክር ቤቱ የ11 ዳኞችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የ11 ዳኞችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፡- የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የ11 ዳኞችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ዘመን 5ኛ የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቋል።
ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የ2018 ዓ/ም እቅድ አፈጻጸም፣ የ2019 ዓ/ም በጀት ዓመት እቅድና ማስፈጸሚያ በጀትን አጽድቋል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎስ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ በሕዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ መትጋት ይገባል።
በክልሉ ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ሕዝብ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብርና በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ክልሉ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ልማት በመለወጥ የገጠሩን አርሶና ከፊል አርብቶ አደር ሕይወት ለማሻሻል ከአመራሩ የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።
በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የታዩትን ጥንካሬዎች በማስፋት በአዲሱ የበጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አፈ-ጉባኤዋ አመልክተዋል።
የምክር ቤቱ ጉባኤም የ11 የጠቅላይ፣ የከፍተኛና የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት መርምሮ በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቋል።