ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ዘመናዊ የከተሜነት የሥነ-ምኅዳር ከባቢ አጎናፅፏታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ውጤታማነት ዘመናዊ የከተሜነት የሥነ-ምኅዳር ከባቢ እንዳጎናጸፋት የከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በከተማዋ እየተካሄዱ ያሉትን የኮሪደር፣ የወንዞችና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አስመልክቶ ከአካባቢ ጥናት አማካሪ ድርጅቶች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የልማት ፕሮጀክቶች ከአካባቢና ከማህበረሰብ ደህንነት ጋር ተጣጥመው እንዲሄዱ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ (EIA) እና ኦዲት ጥናቶች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተቋማቸው ደረጃውን የጠበቀና ተወዳዳሪ ለመሆን የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ከአማካሪ ድርጅቶች የሚገኙ ግብዓቶች ተቋማዊ አሰራሩን ለማዘመንና የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚረዱም ነው የገለጹት።

በባለሥልጣኑ የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ አቶ አብዲ ቀሊ በበኩላቸው፤ አማካሪ ድርጅቶች የሚያቀርቧቸው የጥናት ሰነዶች በጥራትና በሳይንሳዊ ደረጃቸው ብቁ ሊሆኑ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የመድረኩ ዋና ዓላማ የብክለት መጠንን በጥናት በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም