ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት አውደ ርዕዩ ተኪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን የማነቃቃት ሚና ይኖረዋል

አሶሳ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ታምርት አውደ ርዕይ ተኪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን የማነቃቃት አበርክቶ እንደሚኖረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜን 1/2018 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት አውደ ርዕይ ይካሄዳል።

አውደ ርዕዩን አስመልከቶ መግለጫ የሰጡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ  አመንቴ ገሺ አውደ ርዕዩ በክልሉ ተኪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ያነቃቃል።

አውደ ርዕዩ በተጨማሪም በክልሉ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አቅሞች በማስተዋወቅ ወደ ልማት እንዲገቡ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ‎በአውደ ርዕዩ ላይ እንደሚሳተፉ ገልፀው፤ ኢንዱስትሪዎቹ የእርስ በርስ የተሞክሮ ልውውጥ የሚያደርጉበት እና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የሚገመገምበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ታምርት አውደ ርዕይ የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማበረታታት የወጪ ፍላጎትን በራስ ምርት ለመሸፈን የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

‎በክልሉ የማዕድን፣ የግብርና፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የአገልግሎት ዘርፎችን በቅንጅት በመምራት ለኢንዱስትሪው ምቹ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም