በአማራ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ የማጥራትና ዲጂታላይዝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ የማጥራትና ዲጂታላይዝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ የማጥራትና ዲጅታላይዝ የማድረግ የሪፎርም ስራ በተጠናከረ አግባብ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ገለፀ።
በክልሉ ተቋማት የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የሚያስችል የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ የመገንባት የሪፎርም ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህም ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፣ የተገልጋዮችን መጉላላትና እንግልት የሚያስቀር አሰራር እየተዘረጋ መሆኑም ተመላክቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ካሳ አበባው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ የማዘመን ሥራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ለዚህም ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራ በተቀናጀ አግባብ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ የሚያዘምን ነው ብለዋል።
በየደረጃው ወደ አገልግሎት በገቡ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት የሕዝቡን እርካታ እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በአንድ ማዕከል በሚሰጠው አገልግሎትም የተገልጋዮችን እንግልት፣ ድካምና ወጪን ባስቀረ አግባብ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም የሕዝቡን የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአፋጣኝ መመለስ እንደተቻለም አንስተዋል።
የሪፎርሙ አካል የሆነው የመንግሥት ሠራተኛ መረጃ የማሰባሰብ፣ የማጥራትና ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ በተቀላጠፈ አግባብ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ከመጋቢት ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደ ጥረትም ከአጠቃላይ ሠራተኛው 80 በመቶ ያህሉን ማለትም ከ432 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን መረጃ የማሰባሰብና የቆጠራ ሥራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
ይህም በተቋማት ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ከማስቻሉም በላይ ያለውን የሠራተኛ ቁጥር በትክክል ለማወቅ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።