ቀጥታ፡

በምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የሚበጁ የመግባባት ሀሳቦችን በማንሳት እየተመካከርን ነው - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የሚበጁ የመግባባት ሀሳቦችን በማንሳት እየተመካከሩ መሆናቸውን ተመካካሪዎች ገለጹ።

ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በምክክሩ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ እየደረሱ ይገኛሉ።

የምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው ዜጎች በነጻነት በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሀሳባቸውን የሚያንሸራሩበት አካታችና አሳታፊ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ተመካካሪና የማህበረሰብ መሪ ወማ ጌታቸው እንደሚሉትም፤ የምክክር ጉባኤው ሰላማዊትና መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ወርቃማ ዕድልን ፈጥሯል።

በምክክር ሂደቱም አንዱ አንዱን ሀሳብ በቅጡ የሚገነዘብበትን አካታችና አሳታፊ ዕድል መፍጠር የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የሚያጎለብት መግባባት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም በመድረኩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትና ሰላምን የሚያመጣ ውጤት ይገኝበታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።


 

ሌላኛው ተመካካሪ ወጣት አህመድ ኢማም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ይህን የምክክር መድረክ መፍጠሯ የዘመናት የአለመግባባት ችግርን መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጿል።

ይህም አንዱ በአንዱ ጫማ ላይ በመቆም፤ የጋራ ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ መግባባት መፍትሔ መስጠት የሚያስችል የጋራ አሸናፊነት ምክክር እያደረጉ መሆኑን አስረድቷል።

በጉባኤው ላይ በየደረጃው በነበሩ የቡድን ውይይቶችም ላይ ተመካካሪዎች ሀሳባችንን በነጻነት በማንጸባረቅ ለኢትዮጵያ የሚበጁ ሀሳቦችን እያወጣን ነው ሲልም አክለዋል።

ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የወከልን ተመካካሪዎች በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ገንቢ የመግባባት ምክክር እያደረግን ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ሽመልስ ገብረሚካኤል ናቸው።


 

በምክክር መድረኩም ሀገርን ለማጽናት መሠረት የሆነውን ሰላም ሊያመጡ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦችን እያንጸባረቁበት መሆኑን አንስተዋል።

ተመካካሪ ዳርሰማ ሶሪ በበኩላቸው፤ ለሀገር ሁለንተናዊ ሰላምና እድገት የመጀመሪያው ጉዞ የጋራ ምክክር መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያን እድገት ከሚያቀጭጭ የጥፋት አካሄድ ለመላቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገራዊ ምክክር መድረክ መዘጋጀቱም ለትውልድ የሚበጅ መሠረት መጣል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በምክክር ጉባኤውም በተመካከሪዎች መካከል ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያዋጡና የሌሎችንም ሀሳብ በተገቢው መንገድ እየተገነዘብኩ እገኛለሁ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም