ቀጥታ፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦አርቲስት ደበበ እሸቱ ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ  ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ስራ አስኪያጅ አቶ ባረከ ታደሰ ገለጹ።

የአርቲስት ደበበ እሸቱ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር በብሄራዊ ቴአትር ተካሄዷል።


 

በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ  አርቲስቱ  በህይወት ዘመኑ የሰራቸውን ስራዎች እንዲሁም ያገኛቸውን ዕውቅናዎች የሚያሳዩ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይም ተከፍቷል።  

በመርሃግብሩ ላይ የአርቲስት ደበበ እሸቱ ቤተሰቦች፣ የሙያ አጋሮቹ፣ የኪነ ጥብ ቤተሰብ ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ስራ አስኪያጅ አቶ ባረከ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አርቲስት ደበበ በድርሰት፣ በአዘጋጅነት፣ በተዋናይነት  እንዲሁም ስራን በመምራት አርአያነት ያለው ተግባር ፈጽሟል። 

አርቲስቱን መዘከር ሌሎች ባለሙያዎችን ለማፍራት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

አርቲስቱ በዓለም አቀፍ መድረኮችም በብቃት በመተወን እና በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፉ እንዲያድግ በጉልህ የሚጠቀስ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

አዲሱ ትውልድም ከአርቲስቱ ሕይወት ተሞክሮ በመቅሰም ለሙያው የሚያስፈልገውን እውቀት፣ ፈጠራ እና ተሰጥኦ በመላበስ ለውጤት ለመብቃት ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።


 

አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ በበኩሏ፤ አርቲስት ደበበ ለኪነ ጥበቡ እውቀቱንና ጊዜውን ሳይሰስት በመስጠት ለሙያው ያለውን ክብር በተግባር ማረጋገጡን ገልጻለች። 

ተተኪዎችን በማፍራት ረገድም ጉልህ ሚና ማበርከቱን የጠቀሰችው አርቲስቷ፤   የህይወት ልምዱ ሀገር ወዳድነትን፣ፍቅርና መተባበርን የሚያስተምር መሆኑን ተናግራለች።


 

የአርቲስት ደበበ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አቶ አለባችው ደሳለኝ በበኩላቸው፤ አርቲስቱ ለኪነ ጥበቡ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል።

አርቲስቱ ከጥበብ ባሻገር ለሀገሩ ትልቅ ፍቅር እንደነበረው ጠቅሰው፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብም ለሀገሩ እድገት የበኩሉን እንዲወጣና በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደነበራችው ተናግረዋል። 

በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ አርቲስት ደበበ እሸቱን የሚዘክሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ቀርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም