ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን ችግሮችን በጋራ መክረው እንዲፈቱ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን ችግሮችን በጋራ መክረው እንዲፈቱ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል-ነዋሪዎች
ወልቂጤ፤ነሐሴ 12 /2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ መክረው እንዲፈቱ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በጋራ መክሮና ተወያይቶ ለመፍታት የሚያስችል ሀገራዊ ምክክር ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚችሉበትን ትልቅ ተስፋ ከመጣሉ ባለፈ አሳታፊነቱ ጎልቶ የታየበት መሆኑንም ተገልጿል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በተለይ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሳይፈቱ የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ መክረው ለመፍታት ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የየም ዞን ነዋሪ ሰዓሊና ቀራፂ አርቲስት ጨብሳ መጫ እንዳሉት፥ ሃገራዊ ምክክሩ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የመጡ ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን የሀሳብ ብዝሀነትም እየተስተናገደበት ይገኛል።
ምክክሩ ለቆዩ አለመግባባቶች መፍትሔ በመስጠት ሰላምን በዛላቂነት ለማረጋጋጥ ካለው ፋይዳ በተጨማሪ፣ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን የሚኖሩት አቶ ዘውገ ሙሉጌታ በበኩላቸው፥ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ልዩነትና አለመግባባቶችን ለመፍታት በጋራ የሚመካከሩበትን ታሪካዊ ዕድል መፍጠሩን ነው የገለጹት።
ከግል ፍላጎት ይልቅ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚካሄደው ምክክር ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚኖረው አስተዋጾ የጎላ መሆኑን ተናግረው፣ ተለይተው ለውይይት የቀረቡ ስምንት አጀንዳዎችም ለቆዩ ችግሮቻችን መፍትሄ ለመስጠት ወሳኝ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
በቀቤና ልዩ ወረዳ የቀቤና ባህል ማዕከል እና ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ ሃሰን በበኩላቸው፥ በምክክር መድረኩ ኢትዮጵያዊን በጋራ ቁጭ ብለው መምከራቸው በሀገር ጉዳይ ያላቸውን ተሳትፎና አስተዋጾ የሚያጠናክር ነው።
ለዘመናት ሳይፈቱ የቆዩ ውስብስብ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ተወያይቶ ለመፍታትና ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
የምክክሩ ሂደት ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ መካሄዱ ታሪካዊ ዕድል ከመሆኑ ባለፈ በቀደሙ ጊዜያት የነበረውን አግላይነት በማስቀረት የተሻለ ውጤት ይገኝበታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ኢትዮጵያዊያን በጉዳዮቻቸው ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ ሚናው የጎላ ነው ያለው ደግሞ የማረቆ ልዩ ወረዳ ነዋሪ አርቲስት ነጋሽ ሲጃ ነው።
በምክክር ጉባኤው ውይይት እንዲደረግባቸው የተለዩ አጀንዳዎች ለዘመናት ሳይፈቱ የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት ያስችላሉ ብሎ እንደሚያምንም ገልጿል።