ቀጥታ፡

የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት እመርታ የበሽታ ተጋላጭነትን በመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት እመርታ የበሽታ ተጋላጭነትን በመቀነስ ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ ገለጹ።

የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ጤናማ ትውልድን መገንባት የሚያስችል አስቻይ የከተሜነት ምኅዳር መፍጠሩን የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከቢሮ ዕድሳት የተጀመረው የሥራ ከባቢን የማስዋብ ንቅናቄ የመንግሥት ተቋማትን ምቹና ማራኪ ገጽታ ከማጎናጸፍ ባሻገር የከተሞችን ጤናማነት ለማሻሻል ለተከናወኑ የልማት ሥራዎች መነሻ ሆኗል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት በርካታ ከተሞችን በማዳረስ ነዋሪዎች በንጹህ፣ አረንጓዴና ለአካላዊ እንቅስቃሴ ምቹ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ የሚያስችል ዘመናዊ የከተማ ምኅዳር ፈጥሯል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የከተሞች ማራኪ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ ከማዘመን ባሻገር ለጤናው ዘርፍም ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው።

ይህም የከተሞችን የአካባቢና የወንዞችን ብክለት በመቀነስ ከአካባቢ ብክለትና ንጽሕና ጉድለት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተሞችን ውበት ከማስጠበቅ ባሻገር ጤናማ ማህበረሰብን ለመገንባትም የሚያግዝ የሕዝብ ጤና መሠረተ ልማት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት የከተሞች የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ እመርታዊ የልማት ውጤቶች ዘመናዊ የከተሜነት ምኅዳር ከማጎናጸፍ ባሻገር በበሽታ መቆጣጠርም ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የከተሞች የኮሪደር ልማት ስኬቶችም የአረንጓዴ፣ የመንገድና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የስፖርት ባህልን በማሳደግ ጤናማ ትውልድ መገንባት እየተቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት መዲናዋን ውብ ገጽታ በማላበስ ለነዋሪዎች ንጹህ አየር፣ የእግር ጉዞና የአካል እንቅስቃሴ ዕድሎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

ዘመናዊ ከተሜነት ምኅዳርም ከአየርና ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የንጽሕና አጠባበቅ፣ ቆሻሻ አያያዝ፣ የወንዞችን ብክለት ቅነሳና አረንጓዴ ልማትን የማስፋፋት ሥራ የከተማ ጤናማነትን የሚያሻሽሉ የዜጎች የጋራ ኃላፊነቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በቀጣይም ማህበረሰቡ የከተሞች የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የፈጠረውን ይህን የጤና ጥበቃ ዕድል በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በበኩላቸው፤ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የመዲናዋን ውበትና የአኗኗር ምኅዳር ከማሻሻል ባሻገር ለጤናማ ኑሮ የሚያስፈልጉ ዕድሎችን መፍጠሩን ይገልጻሉ።


 

የመዲናዋ ነዋሪ ውበት ደጉ እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የጉንፋንና ከአካባቢ ንጽሕና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና እክሎችን በመቀነስ ለጤናማ አካባቢ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

አቶ ደስታ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ጤናማ ማህበረሰብን ለመገንባት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን አስገኝቷል ብለዋል።


 

የመዲናዋ የመሠረተ ልማት ውጤቶች ነዋሪዎች ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ የሚያስችሉ ዕድሎችን ፈጥረዋል ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መንበረ አግዘው ናቸው።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም