ቀጥታ፡

የአርብቶ አደሩን ማሕበረሰብ ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ ናቸው

ጂንካ፤ ነሐሴ 12/2018(ኢዜአ) ፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፤ በደቡብ ኦሞ ዞን በና-ፀማይ ወረዳ ወይጦ ክላስተር በአርብቶ አደሮች በኩታ ገጠም የለማውን የሽንኩርት ማሳ ጎብኝተዋል።


 

ዶክተር መሪሁን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ከእንስሳት እርባታው በተጨማሪ በእርሻ ስራ በማሰማራት የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው።

የክልሉ መንግስት የአርብቶ አደሮችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ማሕበረሰቡን ከከብት እርባታው በተጨማሪ በእርሻ ስራ በማሰማራት ወደ ብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ የማሸጋገር ስራ በትኩረት በመሰራቱ ውጤቱ መመዝገቡን ነው የተናገሩት።

ለዚህም በኩታ ገጠም እርሻ የተሰማሩ አርብቶ አደሮች ማሳያ ናቸው ያሉት ዶክተር መሪሁን፥ የማህበረሰቡን  ኑሮ ለማሻሻል የሚደረጉ ድጋፎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ነው ያረጋገጡት።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ እምቅ የግብርና አቅም ያለ በመሆኑም ከማህበረሰቡ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ማዋል እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ናቸው።


 

ይህን ሀብት በማልማት አርብቶ አደሩን ከተረጅነት ለማውጣት ሰፋፊ የግብርና ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅትም አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከጠባቂነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር ሀብት በማፍራት ላይ መሆኑን ጠቁመው ፥ የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ በበኩላቸው፤ በዞኑ ያሉ ሀብቶችን በማቀናጀት ለማልማት በተደረገው ጥረት ለውጥ መጥቷል።


 

በአካባቢው የሚገኘውን የወይጦን ወንዝ በመጥለፍ እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃን በማውጣት ከ 2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ሽንኩርት በመስኖ እየለማ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

በዚህም ከ2 ሺህ 700 በላይ አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ማህበረሰቡን ከተረጅነት በማላቀቅ ሀብት እንዲያፈራ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ግብርና ስራ እምብዛም እንደማይታወቅ ጠቁመው የአካባቢው ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ለድርቅና ተያያዥ ችግሮች ተጋላጭ ይሆን እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በበና-ፀማይ ወረዳ ወይጦ ክላስተር የእንጨቴ ቀበሌ አርብቶ አደር የሆኑት ተክሉ ዘውዴ እና መንግስቱ ቦንዳ ፤በኩታ ገጠም ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች አትክልቶችን በማልማት ከእጅ ወደ አፍ የነበረው ኑሯቸው በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።


 

በሄክታር ከ250 እስከ 300 ኩንታል ምርት እያገኙ እንዳሉ ጠቁመው፥ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድም ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም