የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማቶች በአእምሮ እና በአካል የበለጸገ ትውልድን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማቶች በአእምሮ እና በአካል የበለጸገ ትውልድን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተገነቡ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ገጽታን ከመቀየር ባለፈ በአእምሮ እና በአካል የበለጸገ ትውልድን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የከተማዋን መሠረተ ልማት ከዘመኑ ጋር በማስተሳሰር፣ የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ማሻሻልና አረንጓዴ ቦታዎችን በማስፋፋት ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ችለዋል።
ከተማዋን ለቱሪስቶች ማራኪ ከማድረጉም በላይ በወንዞች ዳርቻዎች ላይ የነበሩ የጎርፍ አደጋ ስጋቶችን በመቀነስ ህብረተሰቡ ንጽህናው የተጠበቀ የመኖሪያ እና መዝናኛ ስፍራዎችን እንዲያገኝ አድርጓል።
በዚህም ዘላቂ የከተማ ልማት እውን እንዲሆን በማስቻል የዜጎችን የኑሮ ጥራት ከፍ አድርጓል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ሥራ ከፍተኛ የገጽታ ግንባታ ከመፍጠሩም በላይ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ አካታች ልማት መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሳይ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ የተከናወኑት ግዙፍ የልማት ሥራዎች ለንባብ፣ ለምርምር እና ለህፃናትና ወጣቶች መዝናኛ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በተለይም የቱሪዝም ፍሰትን በማሳደግና የውጭ ምንዛሬ ገቢን በመጨመር ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የተገነቡት መሠረተ ልማቶች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመገንዘብ በባለቤትነት ስሜት ሊንከባከባቸውና ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አንስተዋል።
አልማዝ ባሻ በበኩላቸው፣ መንግሥት በከተማዋ ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች አዲስ አበባን ዘመናዊ፣ ጽዱ እና ለኑሮ ተስማሚ እንዳደረጓት ገልጸዋል።
ሀገር ተረካቢው ትውልድም የእረፍት ጊዜውን በመናፈሻዎችና በስፖርት ማዘውተሪያዎች የሚያሳልፍበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
ይህም መንግስት ለአሁን እና ለቀጣዩ ትውልድ የምትሆን ሀገር እየገነባ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ደስታ መአረንዳ እና አዱኛ ጌትነት እንዳሉት በአዲስ አበባ አሁን ላይ የሚገባትን ውበት እና ክብር መጎናጸፍ ችላለች።
ይህ ሊሆን የቻለው በአእምሮ እና በአካል የበለጸገ ትውልድን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረጉ ሁለንተናዊ የከተማ ልማት ሥራዎች በስፋት በመሰራታቸው መሆኑን አንስተዋል።
የወንዝ ዳርቻ፣ መጽዳት ቤቶችና ቆሻሻ አወጋገድ በመስተካከሉ መጥፎ ሽታዎችን በማስቀረት ለነዋሪዎች፣ ለህፃናት፣ ለሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ለቱሪስቶችም ጭምር ዘመኑን የሚመጥን ከተማ ተፈጥሯል ያሉት ደግሞ ክብሩ ወልደሰንበት እና ወልዱ ግርማ ናቸው።
መንግስት ቀደም ሲል የተዘነጉ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለዜጎች የኑሮ ዘይቤ መሻሻል የሚያደርገው ቁርጠኛ አካሄድ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።