በዞኑ የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደጉ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደጉ ይገኛሉ
ገንዳ ውኃ፣ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን የተገነቡ የድልድይ መሰረተ ልማቶች፣ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንዳስቻሉ ነዋሪዎች ገለጹ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ እና መተማ ወረዳዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከሁለት መቶ አርባ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ እና አምስት የኮንክሪትና ተንጠልጣይ ድልድዮችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉም ተገልጿል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የቋራ ወረዳ ነዋሪ አቶ አያሌው መኮንን እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በክረምት ወቅት ከመተማ ወረዳ ጋር ለመገናኘት አስቸጋሪ እንደነበር ይገልፃሉ።
በአሁን ወቅት ግን በሽንፋ ወንዝ ላይ የተገነባው ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ያጋጥማቸው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር እንደቀረፈላቸው ነው የሚናገሩት።
የመንገድ መሠረተ ልማቱ መገንባት ነዋሪዎቹ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ግንኙት ይበልጥ ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አክለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የመተማ ወረዳ የመሸሃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደስታው ዳኘው በበኩላቸው፣የተገነባው የጠጠር መንገድ ከዚህ ቀደም በክረምትና በበጋ ለመንቀሳቀስ ይደርስብን የነበረውን ችግር የፈታ ነው።
በተለይ በክረምት ወቅት እናቶችና ህጻናት ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ ያጋጥማቸው የነበረውን ከፍተኛ እንግልት እንዳስቀረም ነው ያስረዱት ።
የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀላጠፍና የሸቀጦች አቅርቦት እንዲሻሻል ማድረጉን የገለፁት ደግሞ በቋራ ወረዳ ሽመለጋራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት ደስታው ናቸው።
ቀደም ሲል እናቶች ለወሊድና ለህክምና ወደ ጤና ተቋማት በሰው ሸክም ይወሰዱ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን ተሽከርካሪዎች እስከ መንደራቸው ድረስ ለመግባት በመቻላቸው ችግሩ መቃለሉን ነው የገለጹት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ የዲዛይንና ኮንስትራክሽን አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን አበበ፣ የመንግሥት ትኩረት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከሁለት መቶ አርባ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድን ጨምሮ አምስት የኮንክሪትና ተንጠልጣይ ድልድዮችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን አስረድተዋል።
የተገነቡት መንገዶች ወረዳዎችንና የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በእርስ የሚያገናኙ በመሆናቸው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉንም አቶ ጥላሁን አረጋግጠዋል።