የስራ አጥነትን በስራ ፈጠራ ያሸነፉ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የስራ አጥነትን በስራ ፈጠራ ያሸነፉ ወጣቶች
በጅማ ከተማ አስተዳደር ያለውን የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ፈጠራ ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች በማደራጀት አበረታች እና ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
ግብርና እና የግብርና ውጤቶች ማቀነባበር፣ የእንጨት እና ብረታብረት ስራዎች፣ የጎጆ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት እና ንግድ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ እና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የመሳሰሉት ደግሞ ወጣቶቹ ከተደራጁባቸው መስኮች ዋነኞቹ ናቸው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች እንዳሉት፤ ስራ ማጣት የሚያስከትለውን ተስፋ መቁረጥ በፈጠራ ስራ በመተካት በራሳቸው ስራ ተሰማርተዋል።
በዚህም የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ህይወት ከመቀየር ባለፈ፣ በከተማዋ ለሚገኙ ሌሎች ወጣቶችም የከተማዋን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ ተስፋ ሰጪ ሞዴል መሆን ችሏል።
የከተማዋ ነዋሪ ፎዚያ ከድር ከዓመት በፊት በሥራ ፍለጋ ተስፋ ቆርጣ እንደነበር ትናገራለች።
ዛሬ ግን በከተማዋ በተመቻቸላት የጎጆ ኢንዱስትሪ ዕድል የእንጨት ቅርጻ ቅርጽ ሥራን በመስራት ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች።
ሌላኛው ወጣት አብዱረዛቅ ሸውሞሎ አስተዳደሩ ባመቻቸው የጎጆ ኢንዱስትሪ ስራ ውስጥ ከሶስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት የለውዝ ቅቤ ማምረት ስራ ላይ ተሰማርቷል።
የመስሪያ ቦታን ጨምሮ አስፈላጊው ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ገልጾ፤ የሚያዘጋጁት የምግብ ግብዓት ተፈትሾ ጥራቱ የተረጋገጠ በመሆኑ፣ ምርታቸውን በሙሉ እምነት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።
ይህ ዓይነቱ የጥራትና የድጋፍ ትስስር የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴያቸው ዘላቂ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጾ፤ በዚህም ከራስ አልፎ ለሌሎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።
ጂቱ አብዶ እና ሂክማ መሀመድናስርም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ ናቸው።
ከጓደኞቻቸው ጋር በመደራጀት ሰርተው መለወጣቸውን ገልጸው፤ በዚህም ከራስ አልፈው ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ላይ ይገኛሉ።
መንግስት ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ የሚያስደስት በመሆኑ በቀጣይም የበለጠ ሰርተን ለሌሎች ለመትረፍ እንተጋለን ብለዋል ወጣቶቹ።
በጅማ ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት የስራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ አሸናፊ ግርማ በበኩላቸው በከተማዋ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጎጆ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በ3ሺህ 279 ማህበራት ለ31 ሺህ 659 ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል።
ለማህበራቱ ውጤታማነትም የብድር እና የመስሪያ ቦታን ጨምሮ አስፈላጊ ነገሮች መመቻቸታቸውንም አብራርተዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም 4 ሺህ 100 ማህበራትን በማደራጀት ለበርካቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ጠቅሰው፤ ወጣቶች የሚያነሱትን የገበያ ትስስር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።