ምክክሩ ሰላምን በማፅናት በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ያጠናክራል- የአሶሳ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ሰላምን በማፅናት በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ያጠናክራል- የአሶሳ ከተማ ወጣቶች
አሶሳ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምን በማፅናት በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት የሚያጠናክር መሆኑን የአሶሳ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ ለጉባኤው ስኬት ወሳኝ መሠረት ነው።
ወጣቶች በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በግልጽነትና በስፋት በመወያየት የሚሰጡት የመፍትሔ ሐሳብ፣ የትውልዱን ፍላጎት የሚያንፀባርቅና የሀገሪቱን መፃኢ እድል የሚወስን ነው።
በመሆኑም የምክክር መድረኮች የወጣቶችን ድምፅ በጥልቀት የሚያዳምጡና ተሳትፏቸውን የሚያጎሉ መሆናቸው፣ ሂደቱ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የአሶሳ ከተማ ወጣቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምን በማፅናት በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት እንደሚያጠናክር እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የአሶሳ ከተማ ወጣቶች መካከል ሙስጠፋ አልማሙን እንደገለጸው፤ ምክክሩ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ሰላሟ የተረጋገጠና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠች ሀገርን ለመገንባት ያግዛል።
ይህም የወጣቶችን በሀገር እድገት ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማጉላት ከፍተኛ ዕድል በመሆኑ ለስኬቱ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።
ምክክሩ በመደማመጥና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት መሠረት እንደሚጥል ያላትን ተስፋ የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ወጣት አበባ ሙለታ ናት።
የምክክሩ ውጤትም መሬት እንዲወርድ የድርሻዋን እንደምትወጣም አረጋግጣለች።
የምክክር ጉባኤው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ መካሄዱና በአጀንዳነት የተመረጡትም ጉዳዮች ለሀገር ግንባታ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት እንዳለ አስራት ነው።
ምክክሩ ለሀገር አንድነትና ሰላም ይጠቅማሉ በሚሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር የሀገሪቱን መፃኢ ዕድል የሚወስንና ወጣቶች የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው የሚያደርግ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥርም ያለውን ተስፋ ገልጿል።