ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል
ቁምቢ፤ ነሐሴ 12/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የቁምቢ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በጉባኤውም የሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ተወካዮች፣ በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
ጉዳዩን አስመልክቶ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቁንቢ ወረዳ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል።
በወረዳው የሃሪሮ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ኢብራሂም መሀመድ እንዳሉት፤ በሚዲያ በሚያገኙት መረጃ መሠረት በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ ግልጽና ተስፋ ሰጪ ሂደት ያለው ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።
ምክክሩ የመደማመጥና የጋራ መግባባት ባህል የታየበት፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ዕድልና ተስፋ ያለው በመሆኑ የሀገሪቱን እድገት የሚያጎለብትና ሰላምን የሚያፋጥን ዕድልን እንደሚፈጥርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሁሉም ተመካካሪዎች ለሀገር ይበጃል ያሉትን ሐሳብ በማዋጣት በግልጽነት እየተመካከሩ መሆናቸው ለሀገር ተስፋ ሰጪ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ሁሴን ሙዘሚል ናቸው።
አቶ ሁሴንም ምክክሩ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድልን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፣ ለሀገርና ለሕዝብ የተሻለ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ አቶ አህመድ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር የምክክር መድረክ መካሄዱ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
አቶ አህመድ አክለውም፣ ምክክሩ በሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባትን በመገንባት የሕዝብ አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል።