ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፍትሕ ትራንስፎርሜሽንና ማህበረሰብ ፍትሕ አርአያ የሚሆን ስራ እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽንና የማህበረሰብ ፍትሕ ተግባር በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የሄግ የህግ ኢኖሼሽን ኢንስቲትዩት የኦፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሼከር ፑላ ገለፁ።

የኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሼከር ፑላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በፍትሕ አማራጭ የግጭት አፈታት ሥርዓትን ለመዘርጋት እያከናወነች ያለችው ተግባር የሚደነቅ ነው።

በፍትህ ዘርፍ አበረታች ተግባራት እያከናወኑ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ መሆኗን አንስተው በዘርፉ ያስመዘገበችው ውጤታማ ተግባር ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ፍትሕ ሚኒስቴር ከባህላዊ ዳኝነትና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ያለውን ግንኙነትም አድንቀው፤ በባህላዊ ዳኝነት ወጥና በበቂ መረጃ ላይ የተደገፈ አካሄድ መከተል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመፍታት አስተዋፅኦ እንዳለውም አስረድተዋል።

እ.አ.አ በ2019 የተካሄደው የፍትህ ፍላጎትና እርካታ ጥናት ክፍተቶችን ያሳየ መሆኑን ጨምረው አስታውሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ በበርካታ ሀገራት እንደሚሰራ ጠቁመው በኢትዮጵያ ያዩት የፍትሕ ሚኒስቴር ቁርጠኝነት አርአያነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሲዳማ፣ በአፋር እና በአዲስ አበባ የማህበረሰብ ፍትህ ማዕከላትን በመደገፍ የፍትህ ሥርዓቶችን የማጠናከር ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ላይ እያከናወነች ያለው ተግባር ለዘላቂ ሰላምና ለፍትሕ ተደራሽነት በትኩረት እየሰራች መሆኗን ያሳያል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም